የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማጠናከር ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተገለፀ

የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማጠናከር ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ስራዎችን መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮ-ጣልያን ቢዝነስ ፎረም ዛሬ በጣሊያን ሮም ሲጀመር እንደተናገሩት በሃገሪቱ ውስጥ የኢንቨስትመንት ድባቡን ለውጭ ባለሃብቶች ይበልጥ ሳቢ ለማድረግ የሪፎርም ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በቢዝነስ ፎረሙ የተሳተፉ የኢትዮጵያ ባለሃብቶችም ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስርን ለማጥበቅ፤ በፎረሙ የተፈጠረውን መልካም ዕድል ትርጉም ሰጥተው እንዲጠቀሙበት ማሳሰባቸውን ከኢፌዴሪ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይ የጣሊያን ባለሀብቶችም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የጣሊያን ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ኢማኑላ ዴልሬ በበኩላቸው፤ ለሁለቱ ሃገራት የኢኮኖሚ ትስስር መጠናከር መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡