የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤሌክትሮኒክስ ቪዛ 200 ሺህ መንገደኞችን አስተናገደ

በአገሪቱ እ.አ.አ በ2017 በተዋወቀው የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መንገድ በሯን ለውጭ ጎብኚዎች ክፍት አድርጋለች።

አገልግሎቱ ይፋ ከተደረገበት እለት አንስቶ ጎብኚዎች ከየትኛውም የአለም ክፍል ሆነው በአገልግሎቱ በመጠቀም በቀላሉ ወደ አገሪቱ መግባት ችለዋል።

ይህን ተከትሎ ከ217 አገሮች በአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ 200 ሺህ ጎብኚዎች አገሪቱን ረግጠዋል።

መንገደኞቹ አገልግሎቱን ከ 6፡00 ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በማግኘት ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ያለመጉላላት መስተናገድ መቻላቸውን አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎቱን በመጠቀም አገሪቱን የሚጎበኙ ተጓዥች ቁጥር እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በቱሪዝምና በጉዞ ኢንዱስትሪ ውስጥ ላለነው በጠቅላላ መልካም ዜና ነው” በማለት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የጉዞ ክንውኖችን ቀላልና ቀልጣፋ በማድረግ በኩል ከፍተኛ መሻሻል በማሳየቷ ተጠቃሚነቷ እየጨመረ መጥቷል።

ከኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎቱ በተጨማሪ መንገደኞች የሞባይል መተግበሪያዎችን በመጠቀም የአየር መንገዱን አገልግሎት ማግኘታቸው እድገቱን እንዳፋጠነው ተገልጿል፡፡