ዘምዘም ባንክ በሶስት ወራት ለመሸጥ ካቀደው በላይ አክስዮን መሸጡን አስታወቀ

ዘምዘም ባንክ በሶስት ወራት ውስጥ ለመሸጥ ካቀደው በላይ አክስዮን መሸጥ መቻሉን አስታውቋል፡፡

ከወለድ ነፃ ባንክ አገልገሎት ለመስጠት የተቋቋመው ዘምዘመ ባንክ  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሚያዘው መመሪያ መሰረት የባንክ ስራ ፍቃድ ለማግኘት እንዲቻል የተጠየቀውን የካፒታል ክፍያ ለማሟላት የአክስዮን ሽያጭ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ከ6 እስከ 8 ወራት ጊዜ ውስጥ ባንኩ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

ባንኩ 1 ቢሊዮን ዋጋ ያላቸው 1 ሚሊዮን አክሲዮኖችን አቅርቦ ፤ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሽያጭ ከቀረበው አክስዮን በላይ መሸጡን የዘምዘም ባንክ አደራጅ ኮሚቴ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የአንክስዮን ሽያጩ ከሚፈለገው በላይ ተሸጦ መስከረም 30፣ 2012 ቢጠናቀቅም እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ እንዲራዘም መደረጉን ነው የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ የገለፀው፡፡

ዘምዘም ባንክ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ባለ ሃብቶች በሃገሪቱ የልማት እና የእድገት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያደርጉትን ቀጥተኛ ተሳትፎ የበለጠ ለማጎልበት የሚያስችል እድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ባንኩ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በይዘታቸው ሰፊ የሆኑ አዳዲስ የባንክ አገለግሎቶችን ለደንበኞቹ እንደሚሰጥም ነው የተገለፀው፡፡