የምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች ከሚጠበቀው በላይ በባክቴሪያ የተጠቁ መሆኑ ተገለጸ

ቀን ውስጥ የምንገለገልባቸው ቁሶች ለባክቴሪያ ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው ይላሉ ተመራማሪዎች።

ተመራማሪዎቹ አዲስ በሠራነው ጥናት ደርሰንበታል ባሉት መሠረት፤ አንዳንድ የኤሌክትሮኒክ መገልገያዎች ከመጸዳጃ ቤት መቀመጫ በላይ በባክቴሪያ የተጠቁ ናቸው ብለዋል።

ከነዚህ ቁሶች ውስጥ አንዱ በርካቶች በየእለቱ ሥራቸውን ለመሥራት የሚጠቀሙበት የኮምፒውተር ኪቦርዶች ሲሆን፥ የያዙት የባክቴሪያ ክምችትም ከፍተኛ ነው ብለዋል።

እንደ ተመራማሪዎቹ የዴስክቶፕም ይሁን የላፕቶፕ ኮምፒውተር ኪቦርዶች ከመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ጋር ሲነጻጸሩ 20 ሺህ እጥፍ ቆሻሻ እና በባክቴሪያ የተጠቁ ሆነው ተገኝተዋል።

ይህ ብቻ አይደለም የሚሉት ተመራማሪዎቹ ስማርት ስልካችንም በከፍተኛ ደረጃ በባክቴሪያ የተጠቃ ነው ያለኩ ሲሆን፥ ከመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ጋር ሲነጻጸር በ9 ሺህ እጥፍ የቆሻሻ እና በባክቴሪያ የተጠቃ ሆኖ ተገኝቷል ነው የሚሉት።

ጥናቱን ሲ.ቢቲ ነጌትስ የተባለ የጥናት ቡድን ያካሄደ ሲሆን፥ የጥናቱ አላማም ሰዎች በስራ ቦታቸው ላይ የሚጠቀሟቸው ቁሳቁሶች ምን ያክል በባክቴሪያ የተጠቁ ናቸው የሚለውን ለመለየት ነው ተብሏል።

የጥናት ቡድኑ በየቢሮው በመግባት ከኤሌክትሮኒክ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ ናሙና በመውሰድ በላቦራቶሪ ምርመራ አድርገውበታል።

በዚህ ጥናታቸውም ከሁሉም በላይ የቆሻሻ እና በርካታ ባክቴሪያዎችን ይዞ የተገኘው ኤሌክትሮኒክ መታወቂያ ወይም ባጅ ነው ሲሉ ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል።

በርካታ ባክቴሪያዎች አሉበት በማለት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የኮምፒውተር ኪቦርድ ሲሆን፥ የሞባይል ስልክ እና የኮምፒውተር ማውዝ በተከታይ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በኤሌክትሮኒክስ መገልገያ ቁሶቹ ላይ የተገኘው የባክቴሪያ አይነት “gram-positive cocci” ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ፤ ይህ ደግሞ በኒሞኒያ ውስጥ ከሚገኘው ጋር ተመሳሳይ ነው ሲሉም ያብራራሉ።

ለዚህም ይላሉ ተመራማሪዎቹ፥ ፀረ ባክቴሪያ የሆኑ ማጽጃዎችን በመጠቀም በየእለቱ የቢሮ መገልገያ ቁሶችን ማጽዳት መልካም ነው።(ኤፍ.ቢ.ሲ)