ከመደበኛው እንቅልፍ ሁለት ስአት ማጉደል ጉዳት ያስከትላል

በየቀኑ በቂ እንቅልፍ መተኛት ጤናችንን ለመጠበቅ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ትልቅ መሆኑ አያጠያይቅም።

ይሁን እንጂ ከ8 ስአታት በታች የሚተኙ እና ከልክ ላለፈ ውፍረት የሚዳረጉ እና በመጥፎ አኳኋን (ሙድ) የሚነሱ ሰዎች አሉ።

ተመራማሪዎች ከእንቅልፍ ማጣት ጋር ተያይዞ ከሚከሰቱ ችግሮች ባሻገር ከ8 ስአታት በታች መተኛት በፊት እና ቆዳ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ አረጋግጠዋል።

የለንደን እንቅልፍ ትምህርት ቤት ከቤንሰንስ ፎር ቤድስ ጋር በመተባበር ባደረገው ጥናት ከእንቅልፍ ስአታችን ሁለት ስአታትን መቀነስ በሰውነታችን አቋም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብሏል።

የእንቅልፍ ስአታችንን በመቀነሳችን የተነሳ የሚፈጠሩ ችግሮች በሳምንት ውስጥ እንደሚታይም ነው ያረጋገጡት።

በጥናቱ 11 ሺህ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ሳራሽ ቻልመርስ ለአምስት ቀናት ለስድስት ስአታት ብቻ በመተኛት በየእለቱ የተመለከተቻቸውን ለውጦች መዝግባለች።

ቻልመርስ ካጋጠማት የድካም እና መፍዘዝ ስሜት ባሻገር የማስታወስ ብቃቷ መቀነሱን ተናግራለች።

ከፍተኛ የጣፋጭ ነገሮች ፍላጎት እና እና በፍጥነት የመራብ ስሜትም በአምስቱ ቀናት ውስጥ ማስተናገዷን ነው የገለፀችው።

ከላይ ከተጠቀሱት ለውጦች ሁሉ የከፋው ግን በፊቷ ላይ ያሉ ቀዳዳዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ እና ቀያይ ነጠብጣቦችም በከፍተኛ መጠን መውጣታቸው ነው።

በመሆኑም መደበኛ የእንቅልፍ ስአታችን መሻማት በተለይም የፊት ገፅታችነ የማበላሸት አቅሙ ከፍተኛ ነው ብለዋል ጥናቱን ያደረጉት ተመራማሪዎች።  (ኤፍ.ቢ.ሲ)