የዩናይትድ ስቴትስ ጆን ሆፕኪንስ ብሉምበርግ የጤና ተቋም ይፋ ባደረገው ጥናት በየጊዜው በፓሰፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚከሰተው ኤል ኒኖ ከተባለው አየር ሁኔታ ክስተት ጋር በተያያዘ በአፍሪካ ኮሌራ ሊከሰት እንደሚችል የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ አመለከተ።
ባለፉት አመታት ኤል ኒኖ የምስራቅ ፓሰፊክ ሞቃታማ እንዲሆን እያደረገ መሆኑን የጠቀሰው ጥናቱ፥ በምስራቅ አፍሪካ በአንድ አመት ውስጥ 50 ሺህ ሰዎች በኮሌራ ተስቦ ይያዛሉ ብሏል።
በንጽጽር ኤል ኒኖ በልተከሰተባቸው አመታት ከ30 ሺህ ያነሱ ሰዎች ብቻ በተስቦው እንደሚጠቁ ነው ጥናቱ ያመለከተው፡፡
ተመራማሪዎቹ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በአፍሪካ ከ2000 እስከ 2014 በየአመቱ በ3ሺህ 710 የተለያዩ ስፍራዎች ከ17 ሺህ በላይ በሆኑ ሰዎች ያካሄዱት ምልከታ በመተንተን የተሰራ ጥናት ነው፡፡
አፍሪካ በኤል ኒኖ የተመቱ የአህጉሪቱ ክፍሎች ላይ የኮሌራ ተስቦ ከፍ እንደሚል የጠቀሰው ጥናቱ ፥እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2015 ብቻ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሞት መጠን በአፍሪካ መከሰቱን እና 900 ሰዎች በበሽታው መሞታቸውን የአለም የጤና ድርጅት መረጃን ይጠቅሳል፡፡
የጥናቱ አስተባባሪ ጀስቲን ሌዘር እንደሚሉት ኤል ኒኖ ከመምጣቱ ከስድስት እስከ አስራሁለት ወራት በፊት ይታወቃል፡፡
የኮሌራ ማከሚያ ማዕከላት መኖራቸው ፈጣን እና ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት በመስጠት የሞት ቁጥሩን በ30 በመቶ መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡
በኢኳቶሪያል ፓሰፊክ አካባቢ በኤል ኒኖ ሲከሰት በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ሁኔታ ላይ ለውጥ ከማምጣቱም ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ የዝናብ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
ይህም ክስተት በደረቃማ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ የዝናብ መጠን እንዲቀንስ ይሆናል፡፡
በአንዳንድ ቦታዎች በሚፈጠረው ከባድ ዝናብ ከፍሳሽ ማሳወገጃ ይዞ የሚመጣቸው ቆሻሻዎች የመጠጥ ውሃ ይበክላል፡፡
በሌሎች የአፍሪካ ክፍሎች የድረቅ ሁኔታዎች ንጽሁ የመጠጥ ውሃ ምንጮች እጥረት ስለሚፈጠር የተበከለ ውሃ ለመጠጥ በመጠቀም ወረርሽኙን ያባብሰዋል- (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፡፡