የኤች አይ ቪ ቫይረስ ክትባት ላይ አየተደረገ ያለው ምርምር ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው ተባለ

የኤች አይ ቪ ቫይረስ ክትባት ላይ አየተደረገ ያለው ምርምር ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ገለጹ።

ምርምሩ እድሜያቸው ለአቅመ ሄዋንና አዳም በደረሱ ጤናማ ሰዎችና ጦጣዎች ላይ የተደረገ ሲሆን ክትባቱ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ከፍ ማድረግ እንደቻለ ተገልጸዋል፡፡

የቦስተን ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናታቸው፤ ጥናቱ ከተደረገባቸው ጦጣዎች መካከል ሁለት ሶስተኛ ያህሉ ከኤች አይቪ ባይረስ ጋር ተመሳሳይነት ካላቸው ቫይረሶች መከላከል እንደቻለ ነው የተመላከተው።

ክትባቱ ለ400 ጤናማ ሰዎች የተሰጠ ሲሆን፥ ክትባቱ ከተሰጣቸው 5 ሰዎች አንዱ ላይ የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም በመጨመር ውጤታማ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ወደፊትም ለቫይረሱ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ለሆኑ 2 ሺህ 600 ያህል የደቡብ አፍሪካ እናቶች ክትባቱን ለመስጠት ዕቅድ ተይዘዋል ነው የተባለው፡፡

በዚሁ ጥናት ተስፋ ሰጭ ውጤት የተገኘ ቢሆንም ምንጊዜም በእንስሳትና ሰዎች መካከል ተመሳሳይ ውጤት ሊገኝ እንደማይቻልና የጥናቱን ውጤት ለመግለጽ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ መሆኑን የጥናቱ መሪ ዶክተር ዳን ባሩች ገልጸዋል፡፡

የሰውነትን ከኤች አይቪ ቫይረስ የመከላከል አቅምን የሚያሳድግ ክትባት ተገኘ ማለት ሙሉ በሙሉ ቫይረሱን መቆጣጠር መቻል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ዶክተሩ አስረድተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት 37 ሚሊየን ያህል ህዝብ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖር እና በየዓመቱ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በቫይረሱ እንደሚጠቃ ነው የዩፒአይ ድረ ገጽ የዘገበው፡፡