ትንባሆና መሰል እጾችን የሚጠቀሙ ሰዎች ለመተንፈሻ አካላት ካንሰር ተጋላጭ መሆናቸው ተገለጸ

ትንባሆ እና ሌሎች በትንፋሽ የሚወሰዱ እፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች የመተንፈሻ አካል ላይ ለሚደርስ የካንስር በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን በጥናት ተረጋግጧል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለም ዙሪያ በየአመቱ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች በትምባሆ ምክንያት ህይወታቸውን በየአመቱ ያጣሉ፡፡

ከዚህ ውስጥ ከ6 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት በቀጥታ ትንባሆ አጫሾች ሲሆኑ ወደ ስምንት መቶ ዘጠና ሺ የሚጠጉት ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቂ የሆኑት አልያም ደባል አጫሶች የሚሰኙት ናቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ 1ነጥብ1 ቢሊየን ትንባሆ አጫሶች ያሉ ሲሆን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሲጋራ እና መሰል በትፋሽ ወደ ሰው ሰውነት የሚገቡ አነቃቂ ንጥረ ነገሮችን የሚጠቀሙ ሰዎች አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ሃገራት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ትንባሆ እና ሌሎች በትንፋሽ የሚወሰዱ እንደ ሺሻ ያሉ አደንዛዥ እና አነቃቂ እፆችን የሚወስዱ ሰዎች ከአካላዊ ጤና መጓደል ጀምሮ ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ተጋላጭ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሳንፍራንሲስኮ የተገኘው ጥናትም ይህንን እውነታ የሚያጠናክር ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

ተመራማሪዎቹ ባደረጉት ጥናት መሠረት ሲጋራ አልባ የኤሌክትሪክ ሲጋራ እና ትንባሆ የሚጠቀሙ ሰዎች መተንፈሻ አካል ላይ ለሚከሰት የካንሰር በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ጥናቱን ትንባሆ የሚያጨሱ አሜሪካውያን አዋቂዎች ላይ እ.ኤ.አ ከ2013 እስከ 2014 ከ 32 ሺ 320 ሰዎች ላይ የሽንት ምርመራ እንደተደረገ መረጃው አትቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በጥናቱ ከተሳተፉት ተሳታፊዎች ውስጥ 48 በመቶ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ 61 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ18 አመት እስከ 90 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንድ ተሳታፊዎች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

ከ6ሺህ በላይ የሚሆኑት ማሪዋና ፣ሲጋራ፣ በትንፋሽ የሚወሰዱ አደንዛዥ እፆችና ሌሎች አነቃቂ እፆችን የመውሰድ ልምድ ያላቸው ተሳታፊዎች ሲሆኑ የተገኘው ውጤትም ከመተንፈሻ አካላት ጋር በተያያዘ ለሚከሰት የካንሰር በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት፡፡

በጥናቱ መሠረት ሁሉም ትንባሆ ተጠቃሚዎች ኒኮቲን የተሰኘ ትንባሆ ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር ላይ ጥገኛ መሆናቸው ትንባሆን በተደጋጋሚ ለመጠቀም ይገደዳሉ፡፡በተለይም ጭስ አልባ የትንባሆ አይነቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች የበለጠ ተጠቂ መሆናቸውን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡

ሌላው በጥናቱ የደረሰበት ድምዳሜ ጭስ አልባ እና እንደ ሲጋራ ጥቅም ላይ የሚውሉ በትንፋሽ አማካኝነት ወደ ሰው ሰውነት የሚገቡ እፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች ትንባሆ ከሚጠቀሙ ሰዎች በላይ ለህይወታቸው አስጊ ለሆነ የመተንፈሻ አካል ካንሰር በሽታ ተጋላጭ ተጠቂ መሆናቸውን አመላክቷል ። (ምንጭ: ሲጂቲኤን)