ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የጤና አገልግሎት ሽፋንን በፀሃይ ኃይል በመታገዝ ማሳደግ ተችሏል

ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የጤና አገልግሎት ሽፋንን በፀሃይ ኃይል በመታገዝ ማሳደግ መቻሉ ተገለጸ፡፡

በዓለም ላይ ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም፡፡ ከነዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኃይል አቅርቦት አለማግኘት በዓለም ላይ ለሚገኙ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የጤና እንክብካቤ እንዳያገኙ ያስገድዳቸዋል ተብሏል፡፡

የጤና ክሊኒኮች አገልግሎታቸው መሀከል የቀዶ ጥገና ክፍሎች፣ የሕክምና መጋዘኖች እና ቤተ ሙከራዎች በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

መድኃኒቶችን ለማቀዝቀዝ፣ መብራቶችን ለማብራት እና ሕይወት ለማዳን የሚያስችሉ የሕክምና መሳሪያዎችን ለማንቀሳቀስ አሌክትሪክ ወሳኝ ሲሆን የማያስተማምን የኃይል ምንጭ ሕይወትን አደጋ ላይ እንደሚጥል ይገለፃል፡፡

የፀሐይ ኃይል የኃይል አቅርቦት ለሌላቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየረዳ ይገኛል፡፡

ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ መንግስታት ከተባበሩት መንግስታት የልማት መርሃ ግብር ጋር በመተባበርና የፀሃይ ኃይል በመጠቀም በገጠር የጤና ማዕከሎች እና ክሊኒኮች ውስጥ ቀዶ ጥገናዎች በሻማ ብርሃን የሚካሄዱበትን እንዲሁም የክትባት እና ሌሎች መድሃኒቶች ተገቢ ሙቀት ባለማግኘት የሚበለሹበትን አሰራር ለማስወገድ እንደሚጥሩ ተገልጿል፡፡

የፀሃይ ኃይልን በመጠቀም መድሃኒቶችን ለማቀዝቀዝ፣ የጤና መረጃ ስርዓቶችን ለመጠበቅ፣ ለወሊድ አገልግሎት የተመቻቸ ሁኔታን ለመፍጠር እና አካባቢን የሚጎዳውን የካርበን ልቀት መጠን ለመቀነስ እቅድ እንደተያዘ ነው የተነገረው፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት 405 የጤና ተቋማት በዚህ የፀሃይ ኃይል ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆናቸውን ዘገባው አመላክቷል፡፡ (ምንጭ፡-ዩኤን .ኦርግ)