9ኛው የአፍሪካ ክትባት ሳምንት በጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ ነው

9ኛው የአፍሪካ የክትባት ሳምንት በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡

የአፍሪካ የክትባት ሳምንት በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ "ክትባትን ለማጠናከር በጋራ እንስራ" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ሲሆን የበዓሉ ዋና ዓላማም ክትባት ያለውን ጠቀሜታ ለማህበረሰቡ ለማስገንዘብ፣ ያልተከተቡ ልጆችን ለይቶ የክትባት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግና የማህበረሰብ ንቅናቄ ለመፍጠር ነው ተብሏል፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ ኢትዮጵያ የህጻናትን ሞት በመቀነስ የምዕተዓመቱን የልማት ግብ ከታቀደለት ጊዜ አስቀድማ እንድታሳካ ካስቻሏት መካከል የክትባት አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ በማስፋፋት በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካኝነት ቤት ለቤት በመሄድ ለህጻናት አገልግሎቱን መስጠት በመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ2 እስከ 3 ሚሊየን የሚሆኑ ህጻናት የሚሞቱት በክትባት መከላከል በምንችላቸው በሽታዎች መሆኑን እና ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በክትባት ሽፋን ላይ መሻሻል ማሳየቷንና አዳዲስ የክትባት አገልግሎቶችንም ማቅረብ ችላለች ብለዋል፡፡

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን የክትባት ሳምንት በታሰበው መልኩ ለማሳካት በክልላችን የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች፣ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና አጋር አካላት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ቅንጅት በመፍጠር ትኩረት ሰጥተው መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

የአገሪቱን የክትባት ሽፋን ለማሳደግ ታስቦ በሚካሄደው የአፍሪካ የክትባት ሳምንት ሁሉም ማህበረሰብ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በበዓሉ ላይ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮዎች እና የተለያዩ አጋር ድርጅት ሀላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ የሀይማኖት አባቶች የተገኙ ሲሆን ለጤና ባለሙያዎችም የክትባት አምባሳደርነት የእውቅና ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

(ምንጭ፡- የጤና ሚኒስቴር)