ለ2ኛው ዙር የወባ ማስወገድ ሥራ 200 ወረዳዎች ተለይተዋል – ጤና ሚኒስቴር

በሁለተኛው ዙር የወባ ማስወገድ ስራ የሚከናወንባቸው ወረዳዎች መለየታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጸው በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ 200 ወረዳዎች በቀጣይ የወባ ማስወገድ ስራ ለማከናወን መለየታቸውን አስታውቋል።

የወባ በሽታ ግንዛቤው ባልነበረበት ወቅት እና እንደዛሬው በሽታውን የመከላከል ስራ በስፋት ባልተሰራበት ጊዜ በበርካታ ዜጎች ላይ የከፋ የጤና ጉዳት በማድረስ ለኢኮኖሚዊ ችግር ማጋለጡ ይታወቃል።

በሀገሪቱ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎም  የጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች በሽታውን የመከላከያ መንገዶች በማስተማርም በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ይሁን እንጂ የሀገሪቱ 75 በመቶ የሚሆነው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለወባ ስርጭት ተጋላጭ መሆኑ በሽታው ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፋ አድርጎታል።

ለአብነትም በፈረንጆቹ በ2013 በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 3 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው ተይዘው እንደነበር የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እና የመከላከል ስራዎች በማጠናከር ግን ከ 2 ዓመት በፊት በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ማውረድ ተችሏል።

በሽታውን ከመከላከል አልፎ ሀገሪቱን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 ላይ ከበሽታው ነጻ ለማድረግ የሚያስችል ስራ የጤና ሚኒስቴር ጀምሯል።

በሚኒስቴሩ የወባ በሽታ መቆጣጠር እና ማጥፋት ቡድን አስተባባሪ አቶ መብራህቶም ሀይሌ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ከዚህ ቀደም 239 ወረዳዎች ተመርጠው የወባ ማስወገድ ስራ እየተሰራባቸው ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ደግሞ በቀጣይ የወባ ማስወገድ ስራ የሚከናወንባቸው 200 ወረዳዎች መመረጣቸውን አንስተዋል።

እንደ አለም ጤና ድርጅት መረጃ የወባ ማስወገድ ስራ የሚጀመርባቸው ቦታዎች የበሽታው ስርጭት ዝቅተኛ የሆነባቸው ናቸው።

በዚህም መሰረት በመጀመሪያው ዙር ወደ ማስወገድ ስራ የገቡት በጣም ዝቅተኛ የወባ ስርጭት ያለባቸው ሲሆን በቀጣይም እንዲገቡ የተመረጡት ይህን መስፈርት ተከትሎ ነው ተብሏል።

አቶ መብራህቶም እንዳሉት በቀጣይ ወደ ማስወገድ ስራ በሚገባባቸው ወረዳዎች በሽታውን ለማስወገድ የሚረዱ ግብዓቶችን የማሟላት ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል።

በሽታው ያለባቸው ሰዎች በተለይም ቫይቫይክስ የተሰኘውን ጥገኛ ህዋስ  ድጋሚ እንዳያገረሽ የሚያደርግ ፕሪማኩን የተሰኘውን መድሀኒት የማስገባት ስራዎች ተከናውነዋል  ነው ያሉት ።

ይህ በበሽታው የተያዙ ሰዎች በሽታው ድጋሚ እንዳያገረሽባቸው የሚያደርገው መድሃኒት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ጤና ተቋማት እንዲሰራጭ መደረጉንም ተገልጿል።

በተለይም የማስወገድ ስራ መከናወን የተጀመረባቸው እና በቀጣይ ለመግባት ዝግጅት የተደረገባቸው ላይ  መድሃኒቱን የመስጠት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አቶ መብራህቶም ጠቁመዋል።

ስራውን ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን  እና ወባ የማስወገድ ስራውን ስኬታማ ለማድረግ በወጣው ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱንም አክለዋል።

የወባ ማስወገድ ስራውን ለማከናወንም ለ 3 ዓመታት 18 ሚሊየን ዶላር በጀት ተመድቧል ነው የተባለው።

የወባ ማስወገድ ፍኖተ ካርታው ለ14 ዓመታት የተዘጋጀ ሲሆን፥ ዝግጅቱም የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርትን ያሟላ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።