ባለፉት 9 ወራት 171 ሺህ 685 ከረጢት ደም መሰብሰቡ ተገለጸ

ብሄራዊ የደም ባንክ ባለፉት 9 ወራት 171 ሺህ 685 ከረጢት ደም መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ።

ብሄራዊ የደም ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነበረውን የስራ አፈፃፀም ከ31 በላይ የክልልና የብሄራዊ የደም ባንክ አመራሮች በተገኙበት ገምግሟል።

በስራ አፈፃፀም ሪፖርቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 171 ሺህ 685 ከረጢት ደም መሰብሰብ መቻሉን የብሄራዊ የደም ባንክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል በንቲ ተናግረዋል።

በዚህም የዕቅዱን 82 በመቶ ማከናወን መቻሉን የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ውስጥም 58 ነጥብ 58 በመቶ ያህሉ ወደ ልዩ ልዩ የደም ተዋፅኦ መቀየሩን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም የደም ባንክ አገልግሎት በፋይናንስ ራሱን የሚደግፍበት መነሻ ዶክመንት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

የጥናት ሰነዱም አስተያየት እንዲሰጥበት ለአለም የጤና ድርጅት የጤና ኢኮኖሚክስና በጀት ኢንስቲቲዩት ተልኳል ነው ያሉት።

በተያዘው የበጀት አመት ከአዲስ አበባ የጤና ቢሮ ጋር በመተባበር አንድ ሳተላይት የደም ማሰባሰቢያ ክሊኒክ እንዲከፈት መደረጉን ከብሄራዊ ደም ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

ለዚህ ስራም የሰው ሃይል ምደባ ተከናውኖና ግብዓት ተሟልቶ ሰራተኞች በስልጠና ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡