የደቡብ ክልል ጤና ባለሙያዎች ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ከጤና ሚኒስትሩ ጋር በሀዋሳ ተወያዩ

የደቡብ ክልል ጤና ባለሙያዎች ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ከጤና ሚኒስትሩ ጋር በሀዋሳ ከተማ ተወያዩ፡፡

በውይይት መድረኩ ላይም የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማንን ጨምሮ የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ ላይም በደቡብ ክልል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ለህብረተሰቡ መስጠት ከሚያስፈልገው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት አንፃር አነስተኛ በመሆኑ በክልሉ ለሁሉም የጤና ባለሙያዎች ተጨማሪ የስራ መደብ ለመክፈት የሚያስችል በጀት ለመያዝ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ የትርፍ ሰዓት እና የጥቅማጥቅም ክፍያ ላይ የሚቆረጠውን ግብር ተመጣጣኝ ክፍያ በክልሉ መንግስት እና በየደረጃው ባለው የአስተዳደር እርከን የሚሸፈን እንደሚሆንም የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አስታውቀዋል።

ከ2009 ዓ.ም የደሞዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በክልል የጤና ተቋማት ከዚህ በፊት ወደ ጎን የነበረውን የካሪየር እድገት ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ላይ እንዲሆን መወሰኑንም ገልፀዋል።

በክልሎች እና በፌደራል ተቋማት እየተደረጉ የሚገኙት የተለያዩ የጤና ባለሞያዎች ጥቅማጥቅም ክፍያዎች ወጥ እንዲሆኑ በ2005 ዓ.ም የወጣው የጥቅማጥቅም መመሪያ በደቡብ ክልል የጤና ተቋማት እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቅሰዋል።

በመመሪያው ላይ ያልተካተቱ የሙያ ዘርፎች የተጋላጭነት ክፍያ በአጭር ጊዜ እንዲካተት እንደሚደረግም ነው ያስታወቁት።

የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ደመወዝ በክልሉ በሚገኙ በሁሉም አካባቢዎች ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወጥ እንዲሆን መወሰኑንም አስታውቀዋል።

እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ ሌሎች ያልተፈቱ ችግሮችን ለመፍታት በፌዴራል ደረጃ ከተቋቋመው ግብረ ሀይል ጋር በቅርብት በመስራት በክልሉ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሚደረግ ይሆናልም ብለዋል።