የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል 400 የህክምና ተቋማት በአዲስ መልክ ህክምናውን እንዲሰጡ እየተሰራ ነው

የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል 400 የህክምና ተቋማት በአዲስ መልክ ህክምናውን እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በአገር ደረጃ ያለውን የማህፀን በር ካንሰር ህክምናን ተደራሸነት ለማስፋት የተቀናጀ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የማህፀን በር ካንሰር ተጠሪ የሆኑት ወይዘሮ ታከለች ሞገስ ለኢቲቪ እንደገለፁት ቅድመ ካንሰር ምረመራና ህከምና አሁን ላይ በ230 የህክምና ተቋማት እየተሰጠ ነው።

400 ተጨማሪ የህክምና ተቋማት ህክምናውን እንዲሰጡ ስልጠና በመስጠት ዝግጁ የማድረግ ስራ መሰራቱንም ገልፀዋል፡፡

ህክምናውን ለማካሄድ የሚያስችሉ 1 ሺህ 500 የማህፀን በር ካንሰር መመርመሪያ መሳሪያዎችንም በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን ወ/ሮ ታከለች ተናግረዋል፡፡

የማህፀን በር ካንሰር ወደ ሙሉ ካንሰርነት ካደገ ደግሞ እንደ ጥቁር አንበሳ፣ ጳውሎስ፣ ጅማ ባሉ ሆስፒታሎች የቀዶ ጥገና ህከምናውንና መድሃኒቱን እየሰጡ ነው ተብሏል።

የማህፀን በር ካንሰርን ከሌሎች ካንሰሮች የሚለየው መቶ በመቶ በሽታውን መከላከል እንደሚቻልም ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

እስከ 14 አመት እድሜ ላላቸው ልጃገረዶች መከላከያ ክተባቱን በመስጠት፣ የቅድመ ካንሰር ምርመራውን ለሴቶች በማቅረብ፣ ካንሰር ከሆነ በኋላ ደግሞ ህክምናውን በመስጠት በሽታውን ለመከላከል ሚኒስቴሩ እየሰራ መሆኑም ተመልክቷል።