የህፃናት የመቀንጨር ችግርን ለማጥፋት ያለመ ፎረም ተቋቋመ

የሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነትን በተግባቦትና ህዝብ ግንኙነት ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ፎረም ተቋቋመ፡፡

ፎረሙ በቃልኪዳኑ መሰረት ስርዓተ ምግብ እና ጤናን በማሻሻል ከሁለት ዓመት በታች የህፃናት የመቀንጨር ችግርን በ2022 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በተግባቦት እና ህዝብ ግንኙነት ስራዎች ለማገዝ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ የሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በቅንጅት እየተሰራበት መሆኑን አስታውሰው፣ የቃልኪዳኑን ግብ ከዳር ለማድረስ በምግብና በስርዓተ ምግብ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተግባቦትና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚና የላቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በፎረሙ ምስረታ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ወርቁ በበኩላቸው የመቀንጨር ችግር በሀገር ደረጃ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ጠንካራ የተግባቦት ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ መከወን ይገባል ብለዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በስርዓተ ምግብ ፖሊሲ ላይ ገለፃ አቅርበዋል፡፡

በፎረሙ ላይ የጤና፣ የግብርና፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ፣ የትምህርት፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የሴቶችና ህጻናት ወጣቶች፣ የገንዘብ፣ የትራስፖርት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እንዲሁም ከሰቆጣ ቃልኪዳን ማስተባባሪያ ክፍል በተጨማሪም ከትግራይና አማራ ክልሎች የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተወከሉ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡