ትምባሆ ማጨስ የዓይን ብርሃንን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል ተባለ

ትምባሆ ማጨስ የዓይን ብርሃንን በከፍተኛ ሁኔታ ለጉዳት እንደምዳርግ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች በማጨስ ብቻ እይታቸውን አደጋ ላይ እየጣሉ መሆናቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ተናገሩ።

የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከአምስት ሰዎች መካከል ትምባሆ ማጨስ የዓይን ብርሃንን እንደሚያሳጣ እውቀት ያለው አንዱ ብቻ ነው።

ከማያጨሱ ሰዎች ይልቅ የሚያጨሱ ሰዎች በሁለት እጥፍ የዓይን ብርሃናቸውን የማጣት እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡

የዓይን ህክምና ባለሙያ የሆኑት አይሻ ፋዝላኒ እንደሚሉት "ሰዎች ማጨስና ካንሰር ያላቸውን ግንኙነት በሚገባ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ማጨስ የአይን ብርሃን ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት አይረዱትም።"

የሲጋራ ጭስ አይንን የሚያቃጥልና እይታን የሚጎዳ መራዥ ኬሚካል በውስጡ ይዟል።

ባለሙያዎቹ አክለውም ማጨስ ከስኳር ጋር ተያይዞ የሚመጣ የዓይን ህመምን በማባባስ የደም ስሮችን እንደሚጎዳም ይገልፃሉ።

አጫሾች ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የእይታ መቀነሶች ከማያጨሱት ይልቅ በሶስት እጥፍ ተባብሶ የሚታይባቸው ሲሆን፣ ጥቃቅን ነገሮች ለመለየት ያላቸው ችሎታም ይደክማል።

ዶክተር አይሻ "ማጨስ ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣን የእይታ መድከም በማባባስ ለዓይነስውርነት የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ አጫሾች ማጨስ ለማቆም መወሰን ይኖርባቸዋል" ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ።

ከማያጨሱ ሰዎች ይልቅ የሚያጨሱ ሰዎች በድንገተኛ የዓይን ብርሃን መጥፋት የመጋለጣቸው እድል 16 እጥፍ የላቀ ነው የሚሉት ባለሙያዎች፤ ይህ የሚሆነው ወደ ዓይን የሚሄደው የደም ፍሰት በድንገት ሲቋረጥ መሆኑን ይናገራሉ።

ባለሙያዎቹ አክለውም ማጨስን ማቆም አልያም ማቋረጥ የአይን ብርሃናን ከአደጋ ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰው በየጊዜው ምርመራ ማድረግንም ይመክራሉ። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)