በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢቦላ ታማሚ ተገኘ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በሚኖርባት ጎማ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢቦላ በሽታ መታየቱን ባለስልጣናት ይፋ አደረጉ።

ትላንት እሁድ አውቶቡስ ተሳፍሮ ከሌላ ቦታ ወደ ጎማ የመጣው ፓስተር የኢቦላ በሽታ ተገኝቶበታል በማለት የጤና ጥበቃ ሚንስቴር አሰታውቋል።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በሽታው ወደ ሌሎች የመሰራጨቱ እድል ዝቅተኛ ነው ብሏል።

ከአንድ ዓመት በፊት በዲሞክራቲክ ጎንኮ የጀመረው የኢቦላ ስርጭት እስከ አሁን የ1600 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።

የኢቦላ በሽታ የተገኘበት ፓስተር ከጎማ ከተማ 200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው ቡቴምቦ ከምትሰኝ አነስተኛ ከተማ ነው የመጣው።

ባለስልጣናት ፓስተሩ ምናልባትም ቡቴምቦ ውስጥ በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ሳይኖረው እንዳልቀረ ይገምታሉ።

የሃገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ "በሽተኛው የተለየበት ፍጥነት እንዲሁም በአውቶብሱ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎች በሙሉ በመለየታቸው፤ በጎማ ከተማ በሽታው ሊሰራጭ የሚችልበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው'' ብሏል።

ሹፌሩን ጨምሮ በአውቶብሱ ተሳፍረው የነበሩት 18 ሰዎች ከዛሬ ጀምሮ የጤና ምረመራ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

ከአንድ ዓመት በፊት በጎማ የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝ ይከሰታል በሚል የአካባቢው ባለስልጣናት ቅድመ ዝግጅት ሲያካሂዱ ነበር። በዚህም እስከ 3ሺህ የሚደርሱ የጤና ባለሙያዎች የኢቦላ በሽታ ክትባትን ወስደዋል።

በአፍሪካ ትልቁ የኢቦላ ወረርሽኝ በጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን እአአ ከ2014-16 የተከሰተው ሲሆን፣ 28 ሺህ 616 ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል። ከእነዚህም መካከል 11 ሺህ 310 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።

ኢቦላ በበሸታው ከተያዘ ሰው ጋር የሚፈጠር ንክኪ ዋነኛው የበሽታው መተላለፊያ መንገድ ነው።

ኢቦላ ቫይረስ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃዎች ላይ ትኩሳት፣ ድካም፣ የጡንቻ እና የጉሮሮ ህመም ምልክቶችን ያሳያል።

ከዚያ ማስመለስ፣ ተቅማጥ እና ወጪያዊ እና ውሳጣሚ የደም መፍሰስ ያስከትላል። በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ፈሳሽ ከሰውነታቸው ውስጥ ሲያልቅ ወይም የሰውነት አካል ሥራውን ሰያቆም ለሞት ይዳረጋሉ። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)