የኢቦላ ወረርሽኝን ቀድሞ ለመከላከል የህክምና ባለሙያዎች በመላ ሃገሪቱ መሰማራታቸውን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ለቅድመ መከላከል ስራውም ከ290 በላይ የህክምና ባለሙያዎች በመላ ሃገሪቱ መሰማራታቸውን ነው ኢንስቲቲዩቱ የገለፀው።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፥ ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቅድመ መከላከል እና የቁጥጥር ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በዚህም በቦሌ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ እና ባህር ዳር አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች የተጓዦችን የሰውነት ሙቀት በመለካት የልየታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በየብስ ትራንስፖርት ወደ አገር ወስጥ በሚገቡ መንገደኞች ላይ ደግሞ በ21 የፍተሻ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ክትትል በመደረግ ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተለይም ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚመጡ መንገደኞች ነጻ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እስከ 21 ቀን ድረስ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
እስካሁንም ከ17 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ልየታ የተደረገባቸው መንገደኞች የ21 ቀን ክትትል ተደርጎላቸው ነጻ መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።