መንግስታዊ ያልሆኑ የህክምና ተቋማት የልብ ህክምና እንዲሰጡ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ተቋማቱ በዓመት እስከ 750 ለሚደርሱ የልብ ህመምተኞች ህክምና መስጠት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
የልብ ህመምተኞች በመንግስት ህክምና በስፋት እንዲያገኙ ለማድረግ በጥቁር አንበሳ፣ በመቀሌ እንዲሁም በሀዋሳ ከተማ የልብ ህክምና ማእከላትን በማቋቋም በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የልብ ሀክምና አገልግሎትን ለማስፋት ከሚሰሩት ስራዎች ውስጥ ተጨማሪ ማእከላትን መገንባት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ ከ2 ወር በፊት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግንባታው የተጀመረው ማእከልም አሁን ላይ 15 በመቶ ላይ መድረሱን አሳውቀዋል።
ከኔዘርላንድ መንግስት ጋር በመተባበር በ50 ሚሊየን ዩሮ እየተገነባ የሚገኘው የልብ ማእከሉም በ2 ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አስታውቀዋል። (ምንጭ፡-ኤፍቢሲ)