ኩፍኝ በዲሞክራቲክ ኮንጎ 2700 ህፃናትን መግደሉ ተገለጸ

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከስቶ 2ሺ 700 ህጻናትን መግደሉ ተገለጸ።

በሽታው በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ጋር ሲነጻጸር እጅጉን የከፋና አደገኛ መሆኑም ተገልጿል።

ሰኔ ወር ላይ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ኩፍኝ በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ቢታወጅም በሽታውን ለመግታት የተደረገው ጥረት አናሳ መሆኑን የፈረንሣይ ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ሜድሰ ሶ ፍሮንትዬር ለቢቢሲ ተናግሯል።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሜድሰ ሶ ፍሮንትዬር ተልዕኮ ኃላፊ የሆኑት ካርል ያንሰን እንደተናገሩት ከሃገሪቱ 26 ግዛቶች መካከል 23 በወረርሽኙ ተመትተዋል።

የክትባት አቅርቦት ችግር፣ የንጽህና ጉድለት፣ የግጭቶች መበራከትና የሰዎች መፈናቀል ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋት አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተነግሯል።

"ወረርሽኙ በድንገት የሚከሰት ስላልሆነ፤ አሁን ያጋጠመው ችግር ለዓመታት የተጠራቀመ የግድየለሽነት ውጤት ነው" ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

"አሁን ያጋጠመን የኩፍኝ ወረርሽኝ ባለፉት 10 ዓመታት በላይ ኮንጎ ውስጥ ከታዩት መካከል ትልቁ ነው" ሲሉ አክለዋል።

በሀገሪቱ ያለውን የጤና ችግር ለመግታት ያስፈልጋል ተብሎ ከተጠየቀው 8.9 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ማግኘት የተቻለው 2.5 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሃገሪቱ ውስጥም በዚህ ዓመት ከጥር እስከ ነሐሴ ባሉት ስምንት ወራት ውስጥ ከ2700 በላይ ህጻናት በኩፍኝ ለሞት መዳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ባለፈው ዓመት በኢቦላ ምክንያት ከሞቱት ሰዎች አሃዝ በከፍተኛ ደረጃ ላቅ ያለ ነው ተብሏል።

ያለንበት የፈረንጆች ዓመት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሜድሰ ሶ ፍሮንትዬር 475 ሺህ ለሚጠጉ ህጻናት ክትባት የሰጠ ሲሆን፣ ከ27 ሺህ በላይ ለሚሆኑ በበሽታው ለተያዙ ድጋፍና እንክብካቤ ማድረጉ ተገልጿል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)