መቀንጨርን ለማጥፋት እየሰራ መሆኑን የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ገለጸ

በምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን መቀንጨር ለማጥፋት በተለይ በትምህርት፣ በጤና እና በግብርናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት የአማራ ክልል ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት በምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን መቀንጨር በ2022 ከሀገሪቱ ለማጥፋት በተለይ በአማራና ትግራይ በተከዜ ተፋሰስ ባለ 33 ቀበሌዎች  እንዲሁም  በኦሮሚያ  ክልል ችግሩ ባለባቸው ወረዳዎች እየተሰራ ይገኛል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ተፈራ ቢራራ በክልሉ መቀንጨርን ለማጥፋት በተለይ በትምህርት፣ በግብርናና በጤና ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፅ/ቤቱ በተለይ ለትምህርት ግንባታ፣ ለንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት እና ለጤና ተቋማት ግንባታ በጀት በመመደብ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡

መቀንጨር በ2022 ከሀገሪቱ ለማጥፋት የታቀደውን እቅድ ለማሳካት ከስድስት በላይ ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ያነሱት አስተባባሪው እቅዱ እንዲሳካ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ፕሮጀክት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ ቢገባም፤ የታሰበውን ያህል ውጤት ለማምጣት ባለመቻሉ ከሶስት አመት ሪፖርት ግምገማ በኋላ ማሻሻያዎችን አድርጎ ባለድርሻ አካላትን በማካተት እየሰራ ይገኛል ተብሏል፡፡