በ2050 የወባ በሽታ ከዓለም ሊጠፋ እንደሚችል ጥናት አመላከተ

በ2050 የወባ በሽታ ከዓለም ሊጠፋ እንደሚችል አንድ ጥናት አመላከተ፡፡

በሰው ልጆች ታሪክ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠረውና ሚሊየኖቸን የገደለው የወባ በሽታ በዚህ ትውልድ እድሜ ሊጠፋ እንደሚችል ነው ጥናቱ የጠቆመው።

በየዓመቱ 200 ሚሊየን ሰዎች በወባ በሽታ የሚያዙ ሲሆን፣ ብዙ ህጻናት ደግሞ በዚህ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።

ሪፖርቱ እንደሚለው የወባ በሽታን ማጥፋት እንደ ድሮው የማይታሰብና የሩቅ ህልም አይደለም፤ ነገር ግን በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠርና ክትባት ለማግኘት በየዓመቱ የ2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያስፈልጋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የወባ በሽታን ከማጥፋት ጋር ሲነጻጸር የተጠቀሰው ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

የወባ በሽታ ከአራት የተለያዩ ፕላስሞድየም በሚባሉ የፓራሳይት ዓይነቶች የሚተላለፍ ከባድና ሞት አስከታይ በሽታ ነው። አራቱ ፓራሳይቶች፡ ፕላስሞድየም ፋልሲፓረም፣ ፕላስሞድየም ማላሪዬ፣ ፕላስሞድየም ኦቫሌ እና ፕላስሞድየም ቪቫክስ ናቸው።

በቅርብ ጊዜ የወጣ ሪፖርት በ68 የተለያዩ ሀገራት ያሉ የወባ ትንኞች በተለምዶ አገልግሎት ላይ ይውሉ የነበሩ አምስት መድሃኒቶች ተላምደው እንደማይሞቱ ይነግራል።

ከዚያም በተጨማሪ ፀረ-ወባ የሆኑ መድሃኒቶችም በልምምድ ምክንያት ሃይላቸው እየቀነሰ ነው ተብሏል።

የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ከሶስት ዓመት በፊት የጀመረው ይህ ጥናት በዓለማችን ከወባ በሽታ ጋር በተያያዘ አሉ የተባሉ 41 ተመራማሪዎችን ያካተተ እንደነበር ተገልጿል። እነሱም ወባን የማጥፋት ስራ ምን ያክል ስኬታማ መሆን ይችላል እንዲሁም ምን ያክል ገንዘብ ፈሰስ መደረግ አለበት የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሲሰሩ ነበር ተብሏል።

በዚህም መሰረት እ.አ.አ. በ2050 ዓለማችን ከወባ በሽታ ነጻ መሆን እንደምትችል ተገልጿል። ሪፖርቱም በአይነቱ እጅግ የተለየ ነው እየተባለለት ነው።

በምርምር ስራው ተሳታፊ የነበሩት 'ሰር ሪቻርድ ፊቸም' እንደሚሉት ከዚህ በኋላ በሽታውን ማጥፋት እንደ ድሮው ከባድ አይደለም። '' በአንድ ትውልድ እድሜ በሽታውን ማጥፋት እንደምንችል አረጋግጠናል፤ ወሳኙ ነገር ቁርጠኛ ውሳኔ ነው'' ብለዋል።

በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ስራው እልህ አስጨራሽ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በተለይ ደግሞ በሰሜን ምዕራብ ከሴኔጋል እስከ ደቡብ ምስራቅ ሞዛምቢክ ድረስ ያለው ቀጠና እጅግ አስቸጋሪ ነውም ተብሏል።

በ2050 ወባን የማጥፋት ስራው አሁን በስራ ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀምና በመጪዎቹ ዓመታት አዳዲስ የመከላከያ ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ማሳካት እንደሚቻል ባለሙያዎቹ ተናግዋል።

በሳይንሳዊ መንገድ ወባ አስተላላፊ የሆኑት ትንኞችን በማኮላሸት እንዳይራቡ በማድረግ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ጥናቱ ጠቁሟል።

በጥናቱ እንደተገመተው ወባን በ2050 ለማጥፋት ግን በአጠቃላይ የዓለም ሀገራት በየዓመቱ 2 ቢሊየን ዶላር መሰብሰብ መቻል አለባቸው። ይህን ያክል ገንዘብ በየዓመቱ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ብናውቅም ቁርጠኝነት ከተጨመረበት ማሳካት እንችላለን ብለዋል ተመራማሪዎቹ። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)