በአንድ ቀን 10 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

በሀገር አቀፍ ደረጃ “ህይወት ለህይወት… ደም ለግሰን ህይወት እናድን” በሚል መሪ ቃል በአንድ ቀን 10 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሀገር አቀፍ የደም ስጦታው ቀን ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ይከናወናል ተብሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ለታዳጊ ሀገራት ከሀገራቱ የህዝብ ብዛት 1 በመቶዉ ያህሉ ደም መለገስ እንዳለበት ይገልጻል፡፡

ይህም ማለት በሀገራችን ኢትዮጵያ ቢያንስ 1 ሚሊዮን ደም ለጋሽ መኖር እንዳለበት ያሳያል፡፡

ነገር ግን አሁን ያለዉ ደም ለጋሽ ከ0.3 በመቶ በታች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በ2011 በሀገር አቀፍ ደረጃ 222 ሺህ 434 ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ተሰብስቦ ጥቅም ላይ ዉሏል ተብሏል፡፡

እንደ ኢቢሲ ዘገባ ደም የመለገስ ባህል በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲለመድ ለማድረግና የደም ባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ የተጀመረበትን 50ኛ ዓመት በማስመልከት በአንድ ጀምበር 10 ሺህ ከረጢት ደም በመለገስ ለሚፈልጉት ህሙማን ለማድረስ ታስቦ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

100 ሺህ ሰዎችን በመደበኛ ለጋሽነት በመመዝገብና ቃል በማስገባት በተጨማሪም በ30 ቀናት 3መቶ ሺህ በጎ ፈቃደኞችን ለመፍጠርም ታስቧል፡፡