በአለም ከ3 ሕፃናት አንዱ ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለሚመነጭ የጤና ችግር ተጋላጭ መሆኑ ተገለጸ

በአለም ላይ ከሦስት ሕፃናት መካከል አንዱ የምግብ እጥረት አልያም ከመጠን ባለፈ ውፍረት ችግር ተጠቂ መሆኑን ዩኒሴፍ ገለፀ፡፡

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ የዓለማችን 700 ሚሊየን ሕፃናት መካከል ሲሶ ያህሉ ከምግብ እጥረት ወይም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ጋር በተያያዘ ዘላቂ የጤና ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ማክሰኞ ጥቅምት 4፣2012 ያወጣው አዲስ ጥናት ያመለክታል።

“ሕፃናት በአግባቡ የማይመገቡ ከሆነ ጤንነታቸው የተጎዳ ይሆናል” ሲሉ የሕፃናት መርጃ ድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሄነሪታ ፎር ገልፀዋል፡፡

ዳይሬክተሯ “ጤናማ አመጋገብ በመፍጠር ረገድ እስካሁን አመርቂ ሥራ አልሠራንም” ማለታቸውም ተሰምቷል።

በሪፖርቱ መሠረት በበለጸጉት አገራት ይታዩ የነበሩ ችግሮች አሁን ላይ በድሃ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት መታየት ጀምረዋል።

በጥቅሉ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለማችንን በየዓመቱ 3 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ወጪ ያስወጣታል።

በዓለማችን ድሀ አገራት የሚታየው የሕፃናት መቀንጨር እ.አ.አ ከ1990 እስከ 2005 ባሉት ዓመታት ውስጥ 40 በመቶ ገደማ የቀነሰ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ ዕድሜያቸው አራት ዓመት እና በታች የሆኑ 149 ሚሊየን ሕፃናት በዕድሜያቸው የሚጠበቅባቸውን አዕምሮሯዊም ሆነ አካላዊ ዕድገት ያላስመዘገቡ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል። (ምንጭ:- አልጀዚራ)