ሳምሰንግ ካላክሲ ኖት 7 የአውሮፕላን በረራ አስተጓጎለ

ግዙፉ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7 ስልኮቹ እየፈነዱ በማስቸገራቸው ሁሉንም ስልኮች እንዲመለሱ ማድረጉ ይታወሳል።

ነገር ግን ኩባንያው በድጋሚ አይቷቸው ችግር የለባቸውም በማለት ለገበያ ያቀረባቸውም ስልኮች ጥያቄ እያስነሱ ነው።

በትናንትናው እለትም ጋላክሲ ኖት 7 ስማርት ስልክ በአውሮፕላን ላይ እሳት መፍጠሩ ተሰመቷል።

ዘ ቨርጅ እንደዘገበው ብሪያን ግሪን የተባለው ግለሰብ ስማርት ስልክ ኪሱ ውስጥ መጨስ ሲጀምር የሳውዝዌስት አየር መንገድ አውሮፕላን በረራውን አቋርጦ ለማረፍ ተገዷል።

የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች በሙሉ እንዲወርዱ የተደረገ ሲሆን፥ በእሳት አደጋው ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱም ተነግሯል።

ግሪን ከሁለት ሳምንታት በፊት የገዛው ጋላክሲ ኖት 7 ስልኩ በሳምሰንግ ምንም አይነት ችግር እንደሌለበት ምልክት የተደረገበት መሆኑን አስታውቋል።

ስልኩ መቃጠል ከመጀመሩ በፊት አጥፍቶት(ስዊች ኦፍ) ኪሱ ውስጥ እንዳስቀመጠውም ነው ያስታወሰው።

ከዚያም ከኪሱ አውጥቶ የአውሮፕላኑ ወለል ምንጣፍ ላይ ሲጥለው በደምብ መጨሱን ገልጿል።

ሳምሰንግ ጉዳዩን ለማጣራት ስልኩን መመልከት አለብኝ ብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሳምሰንግ ብቻም ሳይሆን የአፕል ስማርት ስልኮች ተመሳሳይ ችግር እየተሰተዋለባቸው ነው።(ኤፍቢሲ)