ሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7 ስልኮቹን የገዙ ሰዎች ስልኮቹን እንዲዘጓቸው (ተርን ኦፍ እንዲያደርጓቸው) ጠይቋል።
ኩባንያው በቅርቡ ጋላክሲ ኖት 7 ስልኩ አውሮፕላን ላይ መንደዱን ተከትሎ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው።
የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁሉንም የጋላክሲ ኖት 7 ስልኮች ሽያጭ እንደሚያቆም አስታውቋል።
ሳምሰንግ ባለፈው የፈረንጆቹ መስከረም ወር ከባትሪ መፈንዳት ጋር በተያያዘ በቀረበበት ቅሬታ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ስልኮቹን እንዲመለሱ ማድረጉ ይታወሳል።
ለደንበኞቹም የባትሪ ችግሩን አስተካክሎ የመለሳቸው ስልኮች ምንም አይነት ችግር አይገጥማቸውም በማለት ማረጋገጫ መስጠቱም አይዘነጋም።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስተካክለው የተመለሱት ስልኮች ጭምር ተመሳሳይ የባትሪ መፈንዳት እና የመጨስ ችግር እየተስተዋለባቸው መሆኑ እየተነገረ ነው።
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ የሳምሰንግ ጋላክሲ ኖት 7 ስልክ ባለቤት በአውሮፕላን ጉዞ ላይ እያለ ስልኩ እሳት መፍጠሩ መዘገቡ የሚታወስ ነው።
በኬንታኪ ነዋሪ የሆነ ሌላ የስልኩ ተጠቃሚም “ከእንቅልፌ ስነቃ ኩሽና ቤቴ በጋላክሲ ኖት 7 ምክንያት በጭስ ታፍኖ አገኘሁት” ብሏል።
ኩባንያውም “የደንበኞቼ ደህንነት ያሳስበኛል፤ እየተካሄደ ያለው ምርመራ እስኪጠናቀቅም በየትኛውም ሀገር የሚገኙ የኩባንያውን ምርት የሚያከፋፍሉ ተቋማት የኖት 7 ስልክ ሽያጩን እንዲያቆሙ እንጠይቃለን” ብሏል።
“የጋላክሲ ኖት 7 ኦርጅናል ስልክ አልያም በድጋሚ የተሻሻለውን የገዙ ደንበኞቻችን ስልኩን ዘግተው የስልኩን አጠቃቀም መመሪያም ቢያነቡት መልካም ነው” የሚለውም በኩባንያው መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙሃን ኩባንያው የዚህን ስልክ ሽያጭ ከእናካቴው ሊያቆመው እንደሚችል እየዘገቡ ነው።
የቴክኖሎጂ ተንታኙ አንድሪው ሚልሮይ፥ ሳምሰንግ በወሳኝ ስአት ይህ ፈተና እንዳጋጠመው አንስተዋል።
ኩባንያው ከተቀናቃኞቹ ጋር እያደረገ ባለው ፉክክር ድል እየቀናው በመጣበት በዚህ ወቅት በጋላክሲ ኖት 7 የተነሳ የደረሰበት ችግር የኩባንያውን የስማርት ስልክ ገበያ እጅጉን እንደሚጎዳው ነው ሚልሮይ የተናገሩት።
የኖት 7 ኦርጂናል ስልኮችን አውሮፕላን ውስጥ ሀይል መሙላት በበርካታ የአቪዬሽን ባለስልጣናት እና በተለያዩ የአለም ክፍል በሚገኙ አየር መንገዶች መታገዱን አስታውሶ የዘገበው ቢቢሲ ነው።