እየተጠናቀቀ ያለው የአውሮፓውያኑ ዓመት ሞቃታማ ዓመት ሊባል መቃረቡ ተሰማ፡፡
በዓመቱ ዘጠኝ ወራት የተመዘገቡት መረጃዎች በ2015 የተመዘገበውን ሙቀት ሊበልጥ የሚችል ሙቀት ሊመዘገብ እንደሚችል ይጠቁማሉ ተብሏል፡፡
የሙቀቱ መጠን ከባለፈው ዓመት ሊበልጥ እንደሚችል ከ90 በመቶ በላይ እርግጠኛ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡
በዓመቱ ከጥር እስከ መስከረም ወር ድረስ በቅድመ ኢንዱስትሪ ዘመን ከተመዘገበው ሙቀት የአንድ ነጥብ ሁለት ድግሪ ሴልሺየስ ብልጫ አስመዝግቧል፡፡
የሙቀቱ መጠን በዚሁ ከቀጠለ እያደር እንደሚጨምር የዓለም ሜትዎሮሎጂ ድርጅት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለሙቀቱ መጨመር የኤሊኖ ክስተት ከፍተኛውን አስተዋፅዖ ማበርከቱ በዘገባው ተመልክቷል፡፡ የካርቦን ልቀት መጨመርም ሌላው አባባሽ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡
እአአ በ2015 የተመዘገበው የ0.88 ድግሪ ሴልሺየስ ሙቀት እአአ ከ1961 እስከ 1990 ከተመዘገበው ከፍተኛው መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል፡፡ ከ2015 በፊት ባሉት ዓመታ የተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን 0.77 ነበር፡፡
የሙቀቱ መጠን እያደር መጨመር አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ የማቂያ ደወል ነው ተብሏል፡፡ በፓሪስ በተካሄደው ዓለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ መስራት ይገባልም ተብሏል፡፡