የጃፓኗን ፉኩሽማ ከተማ የኒውክሌር ጣቢያ ከራዲዮ አክቲቭ ኬሚካል ለማፅዳት 180 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል ተባለ፡፡
የኒውክሌር ጣቢያው እአአ በ2011 በተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥና የሱናሜ አውሎ ንፋስ ነበር ከባድ ጉዳት የደረሰበት፡፡
ይህን ተከትሎ በጣቢያውና በአካባቢው የፈሰሰውን የራዲዮ አክቲቭ ኬሚካል ቅሪትን ለማፅዳት የጃፓን መንግስት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ኬሚካልን ለማፅዳት 50 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተይዞ ወደ ሥራ ቢገባም ወጭው ከተጠበቀው በላይ ሊንር ችሏል፡፡
የማፅዳቱ ሥራ እንደተጀመረ በሶስት ዓመት ወጭው በእጥፍ ጨምሮ 100 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል፡፡
የታሰበው ሥራና የተያዘው በጀት ወደ መሬት ሲወርድ እንደታሰበው ሳይሆን ቀረ፡፡ በጀቱና ሥራው የሚጣጣም አልሆነም፡፡ ወጭው በጣሙን ናረ፡፡ አሁን ላይ ኬሚካሉን የማፅዳቱ ሥራ 20 ትሪሊዮን የን(180 ቢሊዮን ዶላር) እንደሚፈጅ መንግስት ይፋ አድርጓል፡፡
በወቅቱ የተከሰተው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥና በከባድ ወጀብ የታጀበው አውሎ ንፋስ 18ሺ ያህል ጃፓናውያንን ለሞት ዳርጓል፡፡
በ10ሺ የሚቆጠሩትን ከመኖሪያቸው ያፈናቀለ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህንፃዎችንም ለውድመት ዳርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አራት ሺ መንገዶችን ፣78 ድልድዮችንና 29 የባቡር መስመሮችንም ከአገልግሎት ውጭ አድርጓል፡፡