ቢልጌትስ ለኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መከላከያ መድሃኒት ለመፈብረክ 140 ሚሊዮን ዶላር መደበ

አሜሪካዊው ቢሊዬነር ቢል ጌትስ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መከላከያ መድሃኒትን ለመፈብረክ ለሚደረገው ምርምር 140 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ ተመለከተ ፡፡

ይህ አዲስ የምርምር ሃሳብ ከዚህ በፊት ሲሰጥ የነበረውን የህክምና ዘዴ  የሚቀይር ሲሆን በክርን ውስጥ የሚቀበር መሆኑን ይፋ ሆኗል፡፡

ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ለዚህ አስደናቂ ነው ለተባለለት የህክምና ምርምር አስፈላጊውን ወጪ ይሸፍናሉ ተብሏል ፡፡

ልክ እንደ ወሊድ መቆጣጠሪያ የሚያገለግለው ይህ አዲስ የህክምና ቴክኖሎጂ ክኒኑን በየቀኑ በመውሰድ የሚፈጠረውን መሰላቸት ይቀንሳል ነው የተባለው፡፡

ቴክኖሎጂው አንዴ ክርን ውስጥ ከተቀበረ ለ12 ወራት የሚያገለግል ሲሆን በቀላሉ ቀዶ ጥገና ሳያስፈልግ እንደገና መሞላት እንደሚችል ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ያለው የበሽታው መከላከያ ዘዴ በየቀኑ በእንክብል መልክ የሚወሰድ ሲሆን የአለም ጤና ድርጅት ይህን መድሃኒት እንዲወስዱ የሚመክረው በተለያየ ምክንያት ለበሽታው የከፋ ተጋላጭ ለሆኑ ግለሰቦች ብቻ መሆኑ ይታወቃል (ኢ ብ ኮ )፡፡