ትዊተር በዝቅተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት የሚሰራ “ትዊተር ላይት” መተግበሪያ አስተዋወቀ

ትዊተር በዝቅተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት የሚሰራ አዲስ መተግበሪያ ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።

“ትዊተር ላይት” የሚል መጠሪያ የተሰጠው አዲሱ መተግበሪያ ልክ እንደ “ፌስቡክ ላይት” እና “ሜሴንጀር ላይት” በዝቅተኛ የኢንተርኔት ፍጥነት የሚሰራ ሲሆን፥ መተግበሪያውን ትዊተር ከጎግል ኩባንያ ጋር በመተባባር እንደሰራው ታውቋል።

አዲሱ መተግበሪያ ዝቅተኛ የሆነ የኢንተርኔት ፍጥነት ባለባቸው እና ለኢንተርኔት ዳታ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በሚያስከፍሉ ሀገራት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች አዲስ የምስራች ነው ተብሏል።

መተግበሪያው የኢንተርኔት ዳታን በመቆጠቡ በኩል የተሳካለት ነው የተባለ ሲሆን፥ አገልግሎቱን አንድ ጊዜ ለማስጀመርም አንድ ሜጋ ባይት የኢንተርኔት ዳታ ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

እንደ አዲስ ተሻሽሎ የቀረበው ትዊተር ላይት በሞባይል ስልኮች ላይ እንደሚሰራም ተነግሯል።

እንዲሁም እስካሁን የ2G የኢንተርኔት ኔትዎርክ የሚጠቀሙ ሀገራት የሚገኙ ደንበኞቹ ትዊተርን በቀላሉ እንዲጠቀሙ ለማስቻል መሆኑም ታውቋል።

እንደ ትዊተር ኩባንያ ገለጻ አዲሱን ትዊተር ላይት በ3G ኔትዎርክ ለመክፈት 5 ሰከንድ ብቻ የሚወስድ ሲሆን፥ ከዚህ በፊት ለመክፈት ሲወስድ የነበረውን ጊዜም በ30 በመቶ ማሻሻል ተችሏል።

የኢንተርኔት ዳታንም እስከ 70 በመቶ እንደሚቆጥብም ትዊተር አስታውቋል(ኤፍ.ቢ.ሲ)።