በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ዓለም አቀፍ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ተጠናቀቀ

በኢትዮቴሌኮም ስፖንሰር አድራጊነት የተዘጋጀው 2ኛው ዓለማቀፍ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ/አይሲቲ ኤክስፖ/ በአዲስ አበባ ከተማ ሚሊንየም አዳራሽ ለ4 ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ትላንትና መቋጫውን አግኝቷል፡፡

አውደ ርዕዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ለማሳደግ ወጣቶችን ለማበረታታትና ለማነሳሳት የታሰበ እንደሆነ ተገልጸዋል፡፡

በርካታ ታዋቂ የውጭና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች በወቅታዊ የቴክኖሎጅ ውጤቶች ላይ የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስስር ይፈጥሩበታል፡፡

የኢትዮጵያውያን እጅ ያለበት የፈጠራ ስራ የሆነችው በሮቦት ታሪክ የመጀመሪያዋ የሳውድ አረቢያ ዜግነት ያላት ሶፊያ የአውደ ርዕዩ ማድመቂያ ሆናለች፡፡

ሶፊያ 60 ከመቶ በላይ የሚሆነው አካሏ በኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያዎች የተሰራች ሲሆን ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋርም በአማርኛ ቋንቋ ማውራት መቻሏ ይታወቃል፡፡

በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከተገኙት የፈጠራ ባለሙያዎች መካከል የደህንነት መጠበቂያዎችን ይዘው የቀረቡት ወጣቶች ስራዎቻቸውን ማስተዋወቅ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ባሁኑ ወቅት የመታወቂያ ማጭበርበርን የሚያስቀሩ ቴክኖሎጅዎችንም ይዘው የቀረቡ ያሉ ሲሆን የፈጠራ ስራዎቻቸው ወደ ተጠቃሚዎች በሚፈለገው መልኩ አልደረሰም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በየዓመቱ ከከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች የፈጠራና ምርምር ስራዎቻቸው ከምርትነት ወደ ጥቅም እንድቀየሩ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተገለጸው፡፡ 

ኢትዮጵያ ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት አይሲቲ ኤክስፖ ያዘጋጀች ሲሆን አለማቀፋዊ ኤክስፖ ስታዘጋጅ ግን የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በአሁኑ አውደ ርዕይ ከ100 በላይ ተቋማት ምርቶቻቸውን አሳይተውበታል፡፡ በርከት ያሉ ሰዎችም ጎብኝተውታል ነው የተባለው፡፡