የመንግስት አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ‹‹ኤሌክትሮኒክስ የመንግስት አገልግሎት አውታር›› ሊዘረጋ ነው

ለዜጎች ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ‹‹ኤሌክትሮኒክስ የመንግስት አገልግሎት አውታር›› ሊዘረጋ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ስርዓቱ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው መረጃ ለመለዋወጥ፣ የንግድ ስምምነት ለመፈፀም፣ የንግድ ስራዎችን ለመምራት፣ ለመማርና መንግስታዊ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችላቸው ነው ተብሏል፡፡

የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮችን እንዲሁም ወረዳና ቀበሌን በማስተሳሰር ደህንነቱ የተጠበቀ ቀልጣፋና የማይቆራረጥ አገልግሎት ለመስጠትም የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

አገልግሎቱን ለመጀመር የመሰረተ ልማት ለመገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል ተቋማት ሃላፊዎች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ውይይት እያደረጉ ነው፡፡
ስርዓቱን ለመዘርጋት ዝቅተኛ የኢንተርኔት ግንኙነትና የዋጋው ውድነት እንደ ችግር ተነስቷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ አሁን ያለውን 40 ጊጋ ባይት የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት በሚቀጥሉት አመታት 10ሺ ጊጋ ባይት ለማድረስ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ይህ ማሻሻያ ቀልጣፋና የማይቆራረጥ የመንግስት አገልግሎትን ለመስጠት ሊዘረጋ ለታሰበው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል፡፡ (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)