ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን እድገት ጉባኤን ለማስተናገድ ጥያቄ አቀረበች

ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን እድገት ጉባኤን ለማስተናገድ ጥያቄ አቀረበች፡፡

ጉባኤውን በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በጄኔቫ እንዲያስወስን ግብዣ ቀርቦለታል፡፡

ኮንፈረንሱ በፈረንጆቹ 2021 ጥቅምት ወር የሚካሄድ ሲሆን፣ ከአለም ዙርያ የተውጣጡ ከ5 ሺህ በላይ ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ 

ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ማህበር ምክር ቤት በቀጣይ ሰኔ አጋማሽ በጄኔቫ በሚካሂደው ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ላቀረበችው ጥያቄ ውሳኔውን ያስተላልፋል ነው የተባለው፡፡ 

ጥያቄው በዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ማህበር ምክር ቤት ተወስኖ ጉባኤውን የምታስተናግድ ከሆነ ጉባኤው በአፍሪካ ሲካሄድ የመጀመርያው ይሆናልም ተብሏል፡፡ 

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ የአፍሪካ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ኃላፊ የሆኑትን ጆን ኦሞን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ኃላፊው አለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ለእድገት ጉባኤን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ለማስተባበር ቃል ገብተዋል፡፡

(ምንጭ፡- የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)