ሁዋዌ አንድሮይድን እንዳይጠቀም ገደብ ተጣለበት

ጎግል የስልክ አምራቹ ሁዋዌ ላይ የተወሰኑ የአንድሮይድ መተግበሪያዎችን መጠቀም እንዳይችል እገዳ ጣለ።

በዚህ ውሳኔ መሠረትም የተሻሻሉ የሁዋዌ ስማርት ስልኮች በርካቶች የሚጠቀሟቸውን የጎግል መተግበሪያዎችን መገልገል አይችሉም ማለት ነው።

ይህ ውሳኔ የመጣው የትራምፕ አስተዳደር ሁዋዌን የአሜሪካ ኩባንያዎች ፈቃድ ካላገኙ በስተቀር አብረውት መስራት እንዳይችሉ በሚል ዝርዝር ውስጥ ስሙን ካሰፈረው በኋላ ነው።

ጎግል ባወጣው መግለጫ "ጎግል የአስተዳደሩን ትዕዛዝ በመፈፀምና ያለውን ተፅእኖ በመገምገም ላይ ነው።" ብሏል።

ሁዋዌ ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ይህ ውሳኔ ለሁዋዌ ተጠቃሚዎች ምን ማለት ነው?

ሁዋዌ ከዚህ በኋላ የጎግልን የደህንነት መጠበቂያ ማሻሻያዎችንና የቴክኒክ ድጋፍ አያገኝም። እንዲሁም አዳዲስ ምርቶቹ እንደ ዩ ቲዩብና ካርታዎች የመሳሰሉትን መተግበሪያዎች መጠቀም አይችሉም።

አሁን የሁዋዌ ስማርት ስልኮችን እየተጠቀሙ ያሉ ግን መተግበሪያዎቻቸውን ማሻሻል እንዲሁም የጎግል ፕሌይ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ። ነገር ግን ጎግል አዲስ የአንድሮይድ መተግበሪያ የሚለቅ ከሆነ ሁዋዌ በስልኮቹ ላይ መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ አልተፈቀደለትም።

በሙያው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች "በሁዋዌ የደንበኞች አገልግሎት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት የትራምፕ አስተዳደር ሁዋዌን ከአሜሪካ ተቋማት ጋር ካለ መንግሥት የፈቃድ አገልግሎት ማግኘት ከማይችሉ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ ስሙን አስፍሮታል።

የሁዋዌ ባለስልጣናት የድርጅታቸው ስም አገልግሎት ማግኘት ከማይችሉ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ መግባቱን እንዳወቁ ለጃፓን መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለምልልስ "አስቀድመን ተዘጋጅተንበታል" ብለዋል።

ሁዋዌ ከተለያዩ የምዕራብ ሀገራት የሁዋዌን ስልኮች ቻይና ለስለላ ትጠቀምባቸዋለች በሚል ጥያቄ እየተነሳበት ሲሆን ድርጅቱ ግን ክሱን አጣጥሎታል።

(ምንጭ፡- ቢቢሲ)