ግሎባል ኢኖቬሽን ካታሊስት በኢትዮጵያ ለግማሽ ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዷል

ግሎባል ኢኖቬሽን ካታሊስት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ 500 ሺህ የስራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ መያዙን አስታወቀ።

ይህ የተሰማው የኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ከግሎባል ኢኖቬሽን ካታሊስት መስራችና ስራ አስኪያጅ ካምራን ኢላሂያን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ከመከሩ በኋላ ነው ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የዓለም ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየሰራ ያለው ግሎባል ኢኖቬሽን ካታሊስት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በዓለም ላይ በከፍተኛ የቴክሎጂ ዘርፍ 10 ሚሊየን የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ይነገራል።

ከ10 ሚሊየኑ የስራ ዕድል ውስጥ 5 ሚሊየኑን ለአፍሪካውያን ለመስጠት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።

ግሎባል ኢኖቬሽን ካታሊስት የገንዘብና የስልጠና ድጋፍ በማድረግ ነው የስራ ዕድሉን ለመፍጠር ያቀደው ተብሏል።

ኩባንያው ከስታንፎርድ የኒቨርሲቲ ጋር በመተባር መስከረም ወር ላይ በኢትዮጵያ ስልጠና መስጠት እንደሚጀምርም ይፋ አድርጓል።

ዶክተር ጌታሁን ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለሚወጡ ወጣቶች በቴክኖሎጂ የስራ ዕድል ፈጠራው ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘው እንዲካተቱ እንደሚሰራ የኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።