ፌስቡክ ከ3 ቢሊየን በላይ ሀሰተኛ ገጾችን መዝጋቱን አስታወቀ

ፌስቡክ ከሶስት ቢሊየን በላይ ሀሰተኛ አድራሻዎችን ከመተግበሪያው ማስወገዱን አስታውቋል።

ኩባንያው ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ባደረገው ቁጥጥር ከ3 ቢሊየን በላይ ሀሰተኛ ገጾችን ከመተግበሪያው ማስወገዱን ገልጿል።

አድራሻዎቹ የተዘጉት የተለያዩ የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመተግበሪያው ሲያሰራጩ በመገኘታቸው ነው ተብሏል።

በተመሳሳይ ፌስቡክ ከሰባት ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የጥላቻ ንግግሮችን ከመተግበሪያው መሰረዙን ገልጿል።

እርምጃው የተወሰደው ከፈረንጆቹ ጥቅምት ወር 2018 እስከ መጋቢት 2019 ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በተደረገ ቁጥጥር መሆኑንም ነው ኩባንያው የገለጸው።

ፌስቡክ የወሰዳቸው እነዚህ ሁለት እርምጃዎች ኩባንያው ከምንጊዜውም በላይ በመተግበሪያው የሚሰራጩ ይዘቶችን ለማስተካከል ጠንካራ ስራ እየሰራ መሆኑን የሚያመላክት ነው ተብሏል።

በቀጣይነት ደንበኞች መተግበሪያውን ሃፊነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መልኩ መጠቀም እንዲችሉ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም ተገልጿል።

ለዚህም ኩባንያው በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተለያዩ ቋንቋዎች ሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችንና የሀሰት መረጃዎችን ይዘት ለመገምገም የሚያስችል ማዕከል ለመክፈት እየሰራሁ ነው ብሏል።

(ምንጭ፦ ቢቢሲ)