150 የመንግስት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ ኢንዲሰጡ እየተሰራ ነው

በሚቀጥሉት 6 ወራት 150 የመንግስት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ ኢንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ የማይቆራረጥ አገልግሎት ለዜጎች በመስጠት ዜጎች ወደ አገልግሎት ሳይሆን አገልግሎት ወደ ዜጎች እንዲደርስ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ትግበራ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል፡፡ 

ዜጎች የተቀላጠፈ የመንግስት አገልግሎት እንዲያገኙ እና መንግስት ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማቅረብ እንዲያስችለው ሀሉንም የመንግስት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ 6 ተቋማት አገልግሎታቸውን በኤሌክትሮኒክ መስጠት የጀመሩ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት 6 ወራት 150 የመንግስት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ እንዲሰጡ ይደረጋልም ተብሏል፡፡

በ2020 ዓ.ም 320 የመንግስት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ እንዲሰጡ ለማድረግ እቅድ የተያዘ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት 3 አመታት ደግሞ እስከ ቀበሌ ያሉ የመንግስት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ 

ለትግበራው የአይሲቲ መሰረተ ልማቱ የተሟላ አለመሆን እንደ ችግር የሚነሳ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በተሻለ ፍጥነት በሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡ 

የተግበራ የምክክር መድረኩ የተቋማት አመራሮች ስርዓቱ እንዲዘረጋና ዜጎች የተቀላጠፈ የመንግስት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ለማድረግም ያስችላል ተብሏል፡፡ መረጃው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነው፡፡