የኮሪያው ኩባንያ በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል የመክፈት እቅድ እንዳለው ገለፀ

የኮሪያው ታይውን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል የመክፈት እቅድ እንዳለው ገልጿል፡፡

የኩባንያው ባለቤትና ሊቀመንበር ኪም ታይውንና ከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር ጋር በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ መሰማራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

ኩባንያው በ4ኛው ትውልድ የኢንተርኔት ግንኙነት፤ በትልልቅ መረጃ የመተንተን አቅም ግንባታ፤ በዳመና ማስላትና ሞባይል ቴክሎጂ ዘርፍ የመስራት ፍላጎት እንዳለው ይፋ አድጓል፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል በመገንባት የሰው ሃይል አቅም ግንባታና የኮሪያን ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ የማስተዋወቅ ፍላጎት እንዳለውም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዘማቾች በኮሪያ የሰሩትን ታሪክ አንረሳም ያሉት ልዑካኑ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታንም ለማገዝ ቁርጠኞች ነን ብለዋል፡፡

መንግስት በቴክኖሎጂው ላይ ልዩ ትኩረት ማድረጉን የጠቀሱት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታው ጀማል በከር ለኩባንያው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡/የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር/