ፌስቡክ 5 ቢሊየን ዶላር ሊቀጣ ነው

የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች (ሬጉሌተርስ) ፌስቡክ 5 ቢሊየን ዶላር አንዲቀጣ መወሰናቸው ተገለጸ፡፡

ፌስቡክ ቅጣቱ የተጣለበት የግል ማህደር መረጃን ሳይጠብቅ ቀርቷል በሚል ሲሆን፣ ውሳኔው እስከዛሬ ከተላለፉ የገንዘብ ቅጣቶች ሁሉ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

የፌደራሉ የንግድ ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ የሆነው ካምብሪጅ አናሊቲካ፤ የ87 ሚሊየን የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ ያለ አግባብ ወስዷል በሚል ምርመራ ሲያደርግ ነበር።

ይህ ቅጣት በንግድ ኮሚሽኑ ውስጥ በአብላጫ ድምፅ መፅደቁ ታውቋል።

ፌስቡክም ሆነ የፌደራሉ የንግድ ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የፌደራል የንግድ ኮሚሽን ፌስቡክ ላይ ምርመራውን የጀመረው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ሲሆን፤ በወቅቱ ካምብሪጅ አናላቲካ የተሰኘው የፖለቲካ አማካሪ ድርጅት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን የግል መረጃ በሕገ ወጥ መንገድ ማግኘቱ ተዘግቦ ነበር።

ምርመራው ያተኮረው ፌስቡክ በ2011 የተደረሰውን፤ ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ ያለ ፈቃዳቸው ለሦስተኛ አካል ማጋራት የሚከለክለውን ስምምነት ጥሷል ወይስ አልጣሰም የሚለው ላይ ነበር።

ውስጥ አዋቂዎች ለወል ስትሪት ጆርናል እንዳረጋገጡት፤ ፌስቡክ 5 ቢሊየን ዶላር እንዲቀጣ ተወስኗል። ውሳኔው ግን አሁንም ሪፐብሊካን ኮሚሽነሮችና ዲሞክራቶች መካከል ልዩነትን የፈጠረ እንደነበር መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።

ሪፐብሊካን ውሳኔውን ደግፈው ዲሞክራቶች ደግሞ የተቃወሙ ሲሆን፣ ቅጣቱ ተፈፃሚ የሚሆነው በፍትህ ክፍሉ እንደፀደቀ መሆኑ ታውቋል።

ይህ ግን ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ እስካሁን አልታወቀም።

ፌስቡክና የፌደራል የንግድ ኮሚሽኑ የዜናውን ትክክለኛነት ያላረጋገጡ ሲሆን፣ ነገር ግን ለቢቢሲ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

ቅጣቱ ፌስቡክ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ እስከ 5 ቢሊየን ዶላር ድረስ እንደሚጠብቃቸው ከተናገሩት ጋር ተመሳሳይ ነው።

ይህ ቅጣት እውነት ከሆነ የፌደራሉ የንግድ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ከጣለው ቅጣት ሁሉ ትልቁ ይሆናል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)