የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ስለ ሳይበር ደህንነት ተገቢ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል ተባለ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የመሩትና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የመ/ቤቱ የካውንስል አባላት የተሳተፉበት በሳይበር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው ዛሬ ሀምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ከኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ነው የተሰጠው።

ዓለም የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ መሰረት በማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ስለ ሳይበር ደህንነት ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በአገሪቱ የተቀናጀ የሳይበር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲኖር የኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይህንን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መዘጋጀቱን በኤጄንሲው የሳይበር ድንገተኛ ምላሽ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተመሰገን ገብረ ጻድቅ ስልጠናውን በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል።

ስልጠናው የሳይበር ምንነት፣ የሳይበር ደህንነት፣ የሳይበር ዲፕሎማሲ፣ የሳይበር አንድምታ፣ የሳይበር ጥቃትና ተዛማጅ ርዕሶች ላይ ትኩረት አድርጎ ተሰጥቷል።

በስልጠናው የተሳተፉ የመ/ቤቱ ካውንስል አባላት የሳይበር ቴክኖሎጂ በየጊዜው አዳጊና ተለዋዋጭ ከመሆኑ አንጻር መሰል ተከታታይ ስለጠናዎች በማዘጋጀት ግንዛቤን ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የላከልን መግለጫ ያመለክታል፡፡