በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀናጀ የእንስሳት ሃብት ልማት በኦሮሚያ ክልል ሊጀመር ነው

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የተቀናጀ የእንስሳት ሃብት ልማት በኦሮሚያ ክልል ሊጀመር ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቱን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የገጠር ልማት ሴክተር ሃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቴ እና የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ተካልኝ ቀጄላ ተፈራርመውታል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ቡኖ በደሌ፣ ኢሊባቡር፣ ጅማ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ተግባራዊ የሚደረገው ይህ ፕሮጀክት የወተት ልማት፣ የእንስሳት መኖ ዝግጅት፣ የእንስሳት ማዳቀል እና የስጋ ምርት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው ተብሏል።

በቀጣይ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ፕሮጀክቱን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ስራም ይሰራል ነው የተባለው።

ሰፊ የእንስሳት ሃብት ያለው የኦሮሚያ ክልል የሃብቱን ያክል ተጠቃሚ አይደለም ያሉት ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ ችግሩን ለመቅረፍ በቅንጅት መስራት ይጠይቃል ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፣ የእንስሳት ሀብት ልማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ አርሶ አደሩ ከሃብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር በትኩረት መስራት እንሚጠይቅ ተናግረዋል።

የእንስሳት ሃብት ልማት የቴክኖሎጂ ክፍተቱን ለመሙላት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱን በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጥሬ እቃ፣ ቦታና አምራች የሰው ሃይል መኖሩ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ሲገባም ለ35 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ፕሮጀክቱ በትግራይ ክልል ተግባራዊ ሆኖ የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ሲሆን፣ በቅርቡ በሶማሌ ክልል ወደ ስራ መግባት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሞ ወደ ስራ ተግብቷል፡፡

በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ተግባራዊ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡