‘’ፕሮዴቭኮ’’ የተሰኘው ድርጅት የኢ-ኮሜርስ የንግድ እቅድ አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ለማስረከብ ተስማማ

መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ያደረገው ‘’ፕሮዴቭኮ’’ የተሰኘው ድርጅት የኢ-ኮሜርስ የንግድ እቅድ አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ለማስረከብ ተስማማ፡፡

ድርጅቱ ለኤሌክትሮኒክስ ንግዱ የፖስታ አግልግሎት እንዲዘምን፤ በዚህ ንግድ የሚሳተፉ የግል ድርጅቶችን ለማቋቋም እና የመሰረተ ልማትን ለማሟላት የሚያስችል የአተገባበር እቅዶችን አዘጋጅቶ ለማስረከብ ነው የተስማማው፡፡
የንግድ ስርዓቱ ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተሳሰር የሚተገበርበት መንገድ ማመቻቸትም የስምምነቱ አካል ነው፡፡
ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) እና በፕሮዴቭኮ በኩል ደግሞ ቫንዴን ሂውቨን ፈርመውታል፡፡

ድርጅቱ ወደፊት በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለውም አስታውቋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ) በኢትዮጵያ የሚገነባው የምስራቅ አፍሪካ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ወደ ስራ ገብቶ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጥር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዚህ ዘርፍ አዲስ በመሆኗ የድርጅቱ እገዛ ትልቅ አስተዋኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ (ምንጭ፡-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)