የአፍሪካ የኢኖቬሽን ሳምንት በመጪው ጥቅምት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

የአፍሪካ የኢኖቬሽን ሳምንት ከጥቅምት 17 እስከ 23፣2012 በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አይ ቢ ኤ ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ህብረትና የኖርዌይ ኤምባሲ ሳምንቱን የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። 

የኢኖቬሽን ሳምንቱ የአፍሪካ የቴክኒሎጂ ፈጣሪዎችን ከኢንቨስተሮች ጋር በማስተዋወቅ ወደ ስራ የሚገቡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አህመድን መሃመድ ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም 3 ሚሊየን የስራ እድል ለመፍጠር በያዘችው እቅድ ውስጥ የቴክኖሎጂ የስራ እድል ፈጠራ ትልቁን ድርሻ እንዲይዝ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የግሉ ዘርፍ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ መስራት አላባቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለዚህ መንግስት አስፈላጊው ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የአይ ቢ ኢትዮዽያ የበላይ ጠባቂ የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን ውጤታማ ከሆኑ ባላሃብቶች ጋር ለማገናኘት የኢኖቬሽን ሳምንቱ እንደ ድልድይ ሆና ያገለግላል ብለዋል። 

የኢኖቬሽን ሳምንቱ ከጥቅምት 17 እስከ ጥቅምት 232011 በአዱስ አበባ ሲካሄድ፤ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ከ150 በላይ የቴክኖሎጂ የስራ ፈጣሪዎች ስራዎቻቸውን ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

የአፍሪካ ባለሃብቶችም በሳምንቱ ተገኝተው ወደ ስራ ሊገቡ የሚችሉ ፈጠራዎችን እንዲመርጡና ወደ ስራ እንዲያስገቧቸው አጋጣሚውን ይፈጥራል።

አፍሪካውያን የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ፈጠራዎቻቸውን ወደ ስራ ለማስገባት የገንዘብ ችግር ይገጥማቸዋል። ባለሃብቶችም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሃብታቸውን አያፈሱም የሚሉ ወቀሳዎች ይሰነዘራሉ።  የቴክኖሎጂ ሳምንቱ ይህንን ክፍተት ይሞላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዘገባ ያመለክታል፡፡