ዩቲዩብ የህጻናትን መብት በመጋፋቱ 170 ሚሊየን ዶላር ተቀጣ

ዩቲዩብ ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን የግል መረጃ ያለቤተሰቦቻቸው ፍቃድ በመሰብሰቡ በአሜሪካ የንግድ ተቆጣጣሪ ተቋም 170 ሚሊየን ዶላር ተቀጣ።

የህጻናትን የግል መረጃ በመሰብሰብ ልጆች ላይ ያነጣጠሩ ማስታወቂያዎችን ለማሠራት አውሏል ተብሎ ነው የተከሰሰው።

የአሜሪካው የፌደራል ንግድ ተቆጣጣሪ ተቋም (ፌደራል ትሬድ ኮሚሽን)፤ ዩቲዩብ የህጻናትን የግል መረጃ መብት ጥሷል ብሏል።

የዩቲዩብ ባለቤት የሆነው ጉግል፤ ዩቲዩብ ያሰራቸው ማስታወቂያዎች ህጻናት ላይ ያነጣጠሩ አይደለም ቢልም፤ "ዩቲዩብ ከስድስት እስከ አሥራ አንድ ዓመት ባሉ ታዳጊዎች ዘንድ ተደራሽ ነው" የሚል ማስታወቂያ አሠርቷል።

ስለዚህም 136 ሚሊየን ዶላር ለ'ፌደራል ትሬድ ኮሚሽን' እንዲሁም 34 ሚሊየን ዶላር ለኒው ዮርክ ከተማ እንዲከፍል ተወስኗል።

ከንግድ ተቆጣጣሪ ተቋሙ ኃላፊዎች አንዱ የሆኑት ሮሂት ቾፕራ፤ ዩቲዩብ ከዚህም በላይ መቀጣት ነበረበት ብለዋል። ዩቲዩብ የህጻናት ሙዚቃና ፊልም በመጠቀም ልጆችን "ያለአግባብ አማሏል" ብለዋል።

ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ ልጆች ላይ ትኩረት ያደረገ መርሀ ግብር በግልጽ እንዲያስቀምጥም ተወስኗል።

የዩቲዩብ ዋባ ኃላፊ የሆኑት ሱዛን ዎጂኪኪ እንዳሉት፤ ዩቲዩብ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመጠቀም ለህጻናት የተዘጋጁ መርሀ ግብሮችን ለይቶ ያስቀምጣል።

ኩባንያው የህጻናት ቪድዮ የተመለከቱ ተጠቃሚዎችን መረጃ ሰብስቦ ለማስታወቂያ ግብዓት ማዋሉን እንደሚያቆምም ገልጸዋል።

ጉግል የሰዎችን ላፕቶፕ ወይም ዴስክቶፕ ካሜራ ተጠቅሞ፣ በሚስጥር መረጃ ሰብስቦ፣ መረጃውን ማስታወቂያ ለሚያስነግር ሦስተኛ ወገን ያስተላልፋል በሚል አውሮፓ ውስጥ ክስ ቀርቦበታል።

የጉግል ቃል አቀባይ በበኩላቸው "ያለተጠቃሚዎች ፍቃድ ማስታወቂያ አናሰራጭም" ብለዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)