በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጀማሪዎችን ለመደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

”ተስፋ አይ ኤል ጂ” በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጀማሪዎችን በተለያየ መልክ ለመደገፍ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል፡፡

ድርጅቱ በስዊዘርላንድ የቴክኖሎጂ ጀማሪዎችን የቴክኖሎጂ ሃሳቦቻቸውን ከመነሻ ጀምሮ ወደ ገበያ እስኪገቡ ድረስ የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርግ ነው፡፡

በኢትዮጵያም የቴክኖሎጂ ጀማሪዎች የፈጠራ ሃሳቦቻቸው እንዲዳብሩ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ስልጠና መስጠት፣ ለፈጠራ ባለሙያዎች ስራዎቻቸው ወደ ምርት እንዲገቡ የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ፣ የንግድ እቅድ አሰራር ስልጠና እና የቴክኖሎጂ ልምድ ልውውጥ ማድረግ የስምምነቱ አካል ነው፡፡

”ተስፋ አይ ኤል ጂ” በስዊዘርላንድ ደረጃ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል በኢትዮጵያ የመገንባት እቅድ እንዳለውም ይፋ አድርጓል፡፡

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ጀማል በከር እና ”ተስፋ አይ ኤል ጂ” ፕሬዝዳንት ዳዊት ተስፋየ ተፈራርመዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ጀማል በከር ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግስት የያዘውን የቴክኖሎጂ ዘርፍ የስራ እድል ፈጠራን እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

”ተስፋ አይ ኤል ጂ” የስዊዘርላንድ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር በጋራ እንዲሰሩ የማድረግ እቅድ እንዳለውም ማስታወቁን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡