በኢትዮጵያ የተገነባው የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን አቃቂ ወረዳ ቆፍቱ ቀበሌ የተገነባው የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በትናንትናው ዕለት መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በምርቃቱ ላይ የውሃ፣ መስኖና እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍሬህይወት ወልደሃና፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፣ የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ከደቡብ ኮሪያ ዎአም ፕሮጀክት የሚወከሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ተመርቋል፡፡

ፕሮጀክቱ በደቡብ ኮሪያው የኢኮኖሚክ ዲቨሎምንት ኮኦፕሬሽን ፈንድ በተገኝ የገንዘብ ድጋፍ 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንዲሁም ለመስመር ዝርጋታ፣ ለቆጣሪ ገጠማ እና ለሌሎች መሰል ስራዎች 3.9 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበትም ነው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ የሚጠቁመው ፡፡

ፕሮጀክቱ ከተፈረመ በኋላ የሰርቬንግ፣ የኢንጂነሪንግ፣ የግዥና ስርጭት፣ የግንባታ፣ የኮሚሽኒግ፣ የጥገናና የኮሜርሻል ስራዎችን በማከናወን በአሁን ወቅት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

የሶላር ኃይል የማመንጨት አቅምው 250 ኪሎ ዋትሲሆን፤ ሁለት የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎችም አሉት፡፡ የጣቢው የመጀመሪያ ክፍል 630 የሶላር ፓኔሎችን በመጠቀም እስከ 200 ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል፡፡
.
ሁለተኛው የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ደግሞ 162 የሶላር ፓኔሎችን በመጠቀም 50 ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአማራጭ የኃይል ምንጭ /በሚኒ ግሪድ/ ቴክኖሎጂ 12 የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ በቅርቡ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት መፈራረሙ የሚታወስ ሲሆን፤ በተጨማሪም የ25 ከተሞች ከአፍሪካ ልማት ባንክ ይሁንታ ተሰጥቶ በቀጣይ ሳምንት ለጨረታ ዝግጁ ይሆናል፡፡