የኢትዮጵያና ሩሲያ ጥምር ባዮሎጂካል የምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ  በሚቋቋምበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተካሄደ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም ከሩሲያው አምባሳደር ኤቭጀንሲ ተርክሂን  ጋር ዛሬ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የሩሲያ- ኢትዮጵያ ጥምር ባዮሎጂካል የምርምር  ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ በሚቋቋምበት ሁኔታ ፣ በሩሲያ ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ ፕሮፌሰሮች በተለይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያሉት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያስተምሩና በትምህርት ጥራት ላይ እየተሰራ ያለውን ስራ እንዲደግፉ የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በቆይታቸው ሩስያ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች የምትሰጠውን ነጻ የትምህርት ዕድል እና ቀደም ሲል የነበረውን የቴክኒክና ሙያ የክህሎት የትብብር ስልጠና አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም መክረዋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ውድድሮች ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች እንዲሳተፉ ለማስቻል የሩሲያ  ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሚያግዙበት አግባብ ላይ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና የሩሲያ  ሳይንስ አካዳሚ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡

ከላይ በተነሱት ዘርፎች ላይ አብሮ የመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አምባሳደሩ መግለፃቸውን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡