በአፍሪካ የመጀመሪያው “የስማርት” ስልክ ፋብሪካ በሩዋንዳ ኪጋሊ ተከፈተ

በአፍሪካ የመጀመሪያው ‹‹የስማርት›› ስልክ ፋብሪካ በሩዋንዳ ኪጋሊ ተከፍቷል፡፡

"ማራ ስልክ" የተሰኘው ቡድን የከፈተው የስልክ ማምረቻ ፋብሪካ "ማራ ኤክስ" እና "ማራ ዜድ" የተሰኙ ሁለት አይነት ስልኮችን እንደሚመርት ተገልጿል፡፡

ማራ ኤክስ 190 ዶላር ዋጋ የተተመነ ሲሆን፣ ማራ ዜድ ደግሞ 130 ዶላር ዋጋ ተቆርጦለታል፡፡

"በአፍሪካ የተሰራ" በሚል ገበያውን የሚቀላቀለው ማራ ስልክ በሩዋንዳ እና በአህጉሩ ሰፊ ገበያ ካላቸው ሳምሰንግና ቴክኖ ስልኮች ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡

የማራ ቡድን ባለቤት አሺሽ ጄ. ታካር ከፍተኛ ጥራት ያለው ስልክ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ከጥቂት አመታት በኋላ በአህጉሩ ገበያ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ የመውጣት ሃሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካውን በአፍሪካ ብቸኛው "የስማርት ስልክ አምራች" ሲሉም ጠርተውታል፡፡
24 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት ፋብሪካው በፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ተመርቆ በይፋ ተከፍቷል፡፡ (ምንጭ፡- africanexponent.com)