ትዊተር በስህተት ኢሜል አድራሻዎችን ለማስታወቂያ በመጠቀሙ ይቅርታ ጠየቀ

ትዊተር በስህተት ደንበኞቹ ለአካውንታቸው ደህንንት በሚል ያስገቡትን ኢሜል አድራሻና የስልክ ቁጥር ለማስታወቂያ በመጠቀሙ ይቅርታ ጠየቀ።

ኩባንያው እንዳለው ሶስተኛ ወገን ማስታወቂያ ድርጅቶች የተለዩ የትዊተር ተጠቃሚዎችን ዝርዝር መረጃዎች በመጠቀም፣ ተጠቃሚው መረጃው በዚህ መልክ ጥቅም ላይ እንዳይውል ፍላጎት ሳይኖረው፣ ማስታወቂያ ልከውላቸዋል።

ትዊተር በመግለጫው "ምን ያህል ሰው በዚህ ምክንያት እንደተጎዳ ማረጋገጥ አልቻልንም" ያለ ቢሆንም ቢቢሲ ግን በመላው ዓለም ያሉ የትዊተር ተጠቃሚዎች በዚህ ጉዳይ ሰለባ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ብዙ ጊዜ ኩባንያው ደንበኞቹን በቀጥታ ለማግኘትና እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን ለማስተላለፍ ፈጣን አይደለም።

ኩባንያው ችግሩ መቼ እንደተፈጠረ ያለው ነገር የለም። ነገር ግን እኤአ ከመስከረም 17 (ከ21 ቀን በፊት) ጀምሮ መሆኑን ገልጧል።

ድርጅቱ አክሎም ለደህንንት ሲባል የተሰበሰቡ የስልክና የኢሜል አድራሻዎችን ለማስታወቂያ ከአሁን በኋላ እንደማይጠቀም አስታውቋል።

ትዊተር በመላውዓለም በየቀኑ 139 ሚሊየን ተጠቃሚዎች ሲኖሩት ማስታወቂያ በገፃቸው ላይ እንደሚለቀቅም ይናገራል።

ትዊተር ለማስታወቂያ አስነጋሪዎች በግላቸው ተሰብስቦ በእጃቸው የሚገኙ የኢሜል አድራሻዎችን እርሱ ጋር ካሉ አድራሻዎች ጋር በማመሳከር ማስታወቂያ በገፃቸው ላይ ይለቅቃል።

ይህ አሰራር በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ኩባንያዎች ዘንድ የተለመደ ሲሆን በዚህ ከምርቶች ጋር የበለጠ ቅርበትና ትስስር ያላቸውን የተመረጡ ደንበኞችን ታላሚ ያደረገ የማስተዋወቂያ ስልት ተደርጎ ይወሰዳል።

አሁን ግን ትዊተር በመግለጫው ላይ እንዳሰፈረው ከማስታወቂያ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ኢሜል አድራሻ ከማመሳከር ይልቅ በቀጥታ ተጠቃሚዎች ለአካውንታቸው ደህንነት የተጠቀሙትን ስልክና ኢሜል አድራሻ በጅምላ ለማስታወቂያ አገልግሎት መዋሉን ነው።

"የማስታወቂያ ድርጅቶች የገበያ ዝርዝራቸውን ሲያስገቡ እኛ ትዊተር ላይ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸውን ደንበኞች ለደህንነት ማስጠበቂያ ያስገቡትን ስልክ ወይንም ኢሜል አድራሻ እናዛምዳለን። ይህ ደግሞ ስህተት ነው፤ ለዚህም ይቅርታ እንጠይቃለን" ብሏል ኩባንያው።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ፌስቡክ ደንበኞቹ ለደህንነታቸው ሲሉ የተጠቀሙትን የኢሜል አድራሻ ለማስታወቂያ ተጠቅሞበታል በሚል ጠንከር ያለ ትችት ተሰንዝሮበት ነበር።

ፌስቤቡክ ግን ጉዳዩን በስህተት ነው ሲል አልገለፀውም።