በበጀት ዓመቱ 152 የመንግስት አገልግሎቶች በኦንላይን እንዲሰጡ ይደረጋል ተባለ

በዘንድሮ በጀት ዓመት 152 የመንግስት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ እንዲሰጡ ይደረጋል ተባለ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የመንግስት ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በባሉበት ግልጋሎት (የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት) እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችላቸውን የምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተቋቋመው ብሔራዊ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መተግበሪያ ፕሮጀክት፣ አሁን ያለበት ሁኔታ፣ ያጋጠሙ ችግሮችና እቅዶች ቀርበውና ተገምግመው ወደ ፊት አገልግሎቱን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ሲናሞ (ዶ/ር ኢንጂ.)፤ እስከ አሁን በፕሮጀክቱ 126 አገልግሎቶች ለምተው በ34 ተቋማት ወደ ትግበራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በያዝነው አመትም 152 አገልግሎቶችን እንዲለሙ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።
የመብራት፣ የኢንተርኔትና የኔትወርክ ውስንነቶች፣ የተሟላና ወቅቱን የጠበቀ ግንዛቤ አለማግኘት፣ የመስሪያ ቤቶችና ደንበኞች ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የቁርጠኝነት አናሳ መሆን የአገልግሎቱ ተግዳሮቶች መሆናቸው በመድረኩ ተነስቷል፡፡

የባሉበት ግልጋሎት (የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት) ፈጣን፣ ውጤታማና ዘመናዊ የሆነ አሰራር በመሆኑ ጊዜን፣ ወጪንና ጉልበትን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡

የተለያዩ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት በባሉበት ግልጋሎት (የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት) እንዲሰጡ ለማድረግና ወደ ትግበራ እንዲገቡ የሚያስችላቸውን የስምምነት ፊርማ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራመዋል፡፡

መድረኩ በዋናነት የተዘጋጀው አሰራሩን የሚጀምሩ አዳዲስ ተቋማት እውቀት ኖሯቸው አግልግሎቶቻውን እንዲያዘምኑና የተገልጋዮቻቸውን ፍላጎት ማርካት እንዲያስችላቸው መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡